null Standing committee of the House Convinced the Gedabo irrigation project to finish the rest of the project and benefit the farmers around it.

የጊዳቦ መስኖ ልማት ፕሮጀክት ግድብ ግንባታ ቀሪ ስራ ተጠናቅቆ በዙሪያው ያሉትን አርሶ አደሮች ተጠቃሚ ማድረግ ይገባዋል ሲል በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የተፈጥሮ ሃብት ልማት፣ መስኖና ኢነርጅ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ አሳሰበ፣

ቋሚ ኮሚቴው ሰሞኑን በደቡብ ክልል ሲዳማ ዞንና በኦሮሚያ ክልል ምዕራብ ጉጅ ዞን አዋሳኝ ላይ የሚገኘውን የጊዳቦ መስኖ ልማት ፕሮጅቸት ግድብ ግንባታ አፈጻጸም ተመልክቷል፡፡

ፕሮጀክቱ ለአካባቢው ማህበረሰብ ያበረከተውን አስተዋጽኦ፣ ሊያለማ የሚችለውን የማሳ ስፋት በሄክታር፣ የበጀት አፈጻጸሙንና ከባለድርሻ አካላት ጋር ያለውን ቅንጅት የተመለከቱ ጥያቄዎችን ቋሚ ኮሚቴው ለፕሮጀክቱ ተጠሪ መሀንዲስ አንስቷል፡፡

የፕሮጀክቱ ተጠሪ መሀንዲስ አቶ ያህያ አህመድ ፕሮጀክቱን አስመልክተው ማብራሪያ በሰጡበት ወቅት እንዳሉት ፕሮጀክቱ የተጀመረው በ2002 በጀት አመት እንደሆነና በሁለት አመት ውስጥ ተጠናቅቆ ለህብረተሰቡ አገልግሎት እንዲሰጥ ታስቦ የነበረ ቢሆንም በዲዛይን ማሻሻያና በተጨማሪ ስራዎች ምክንያት እስካሁን ማልማት አልጀመረም ብለዋል፡፡

ፕሮጀክቱ ሲጀመር 7ሺ ሄክታር ማሳ እንዲያለማ ታስቦ እንደነበርና ቀስ በቀስ በተደረገ ጥናት 13ሺ ሄክታር እንዲያለማ በመደረጉ ለአፈጻጸሙ መዘግየት ምክንያት መሆኑን የጠቀሱት ተጠሪ መሀንዲሱ የአካባቢው አርሶ አደሮች ከአርብቶ አደር ወደ አርሶ አደርነት የመለወጥ ፍላጎታቸው እያደገ በመምጣቱ የሚመለከታቸው አካላት የፕሮጀክቱ ተጨማሪ ስራዎች በፍጥነት ተጠናቅቀው የአካባቢው ልማት እንዲፋጠን ማድረግ ይጠበቅባቸዋል ብለዋል፡፡

ፕሮጀክቱን ለማጠናቀቅ ወደ 707 ሚሊዮን ብር እንደሚያስፈልግ የገለጹት መሀንዲሱ ግድቡ ስራ ሲጀምር ከመስኖ ልማት በተጨማሪ ለአሳ እርባታ ስራም እንደሚያገለግል አስታውሰው ይህ ከፍተኛ ወጪ የወጣበትና ለአገሪቱም እድገት ጉልህ አስተዋጽኦ ሊያበረክት የሚችለው ፕሮጀክት ጥበቃ ጉዳይም ትኩረት ሊሰጠው እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡

ቋሚ ኮሚቴው በበኩሉ በሰጠው አስተያት እንዳለው የጊዳቦ መስኖ ልማት ግድብ ፕሮጀክት ከአካባቢው ዝናብ አጠርነት አኳያ ሲታይ የስነ-ምህዳሩን ሚዛን በመጠበቅም ይሁን የማህበረሰቡን ኑሮ በማሻሻል በኩል ጠቀሜታው የጎላ በመሆኑ የውሃ፣ መስኖና ኢነርጅ ሚኒስትርም ይሁን ሌሎች የሚመለከታቸው አካላት ከፍተኛ ትኩረት ሰጥተው ቀሪ ስራዎቹ እንዲጠናቀቁ በማድረግ የታለመለትን አላማ እንዲያሳካ ማድረግ ይጠበቅባቸዋል ብሏል፡፡

ኮንትራክተሩ የኢትዮጵያ ኮንስትራክሽን ስራዎች ኮርፖሬሽን ከፍተኛ ልምድ ያካበተና አገር በቀል መሆኑ ለግንባታው ጥራትም ይሁን አቅምን ለመገንባት የተሻለ መሆኑን የጠቆመው ቋሚ ኮሚቴው ነገር ግን የአካባቢው አርሶ አደሮች በግድቡ ግንባታ ደስተኞች ቢሆኑም መጠቀም ባለመቻላቸው ቅሬታ እያሰሙ በመሆኑ በፍጥነት ተጠቃሚ እንዲሆኑ ማድረግ ትኩረት ሊሰጠው እንደሚገባ አስታውሶ በግድቡ ዙሪያ ያለው አብዛኛው መሬት በደን የተሸፈነ በመሆኑ የማሳ ዝግጅቱና ወጣቶችን የማደራጀት ስራው በተመሳሳይ ትኩረት ሊሰጣቸው ይገባል ብሏል፡፡

በሌላ ዜና ቋሚ ኮሚቴው ገናሌ-ዳዋ-ይርጋለም 400KB እና የሐዋሳ የኃይል ማስተላለፊያ ፕሮጀክቶችን ተመልክቷል፡፡

ፕሮጀክቶቹ ከጊቤ ቁጥር-3 የኃይል ማመንጫ ግድብ ተቀብለው ለአዋሳ ኢንዱስትሪ ፓርክና ለአካባቢው የሚያስተላልፉ መሆናቸውን ያስረዱት የፕሮጀክቱ አስተባባሪ አቶ ታምሩ ባቱ ፕሮጀክቱ ለእውቀት ሽግግር ያበረከተውን አስተዋጽኦ አስታውሰው ግንባታው ቢጠናቀቅም የማሰራጫ መስመር በሚዘረጋባቸው አካባቢዎች ህገ-ወጥ የቤት ግንባታ በመስፋፋቱ አፈጻጸሙን አዘግይቶታል ብለዋል፡፡

የአካባቢው አመራሮች በበኩላቸው ችግሩን ለመፍታት ከህብረተሰቡ ጋር ተቀራርበን እየሰራን በመሆኑ ፕሮጀክቱ በቅርቡ ተጠናቅቆ ወደ ተግባር ይገባል ብለዋል፡፡