null State of Emergency inquiry Board has officially begun operations.

የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ መርማሪ ቦርድ ዛሬ ሥራውን በይፋ ጀመረ፡፡

ዜና ፓርላማ ሚያዝያ 5/2012ዓ/ም፡- የኢፌዴሪ የህዝብ ተወካዮች /ቤት ዋና አፈ ጉባዔ የተከበሩ አቶ ታገሰ ጫፎ  በተገኙበት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ አፈፃፀም መርማሪ ቦርድ ሥራውን ዛሬ በይፋ ጀምሯል፡፡

የተከበሩ አቶ ታገሠ ጫፎ ቦርዱን በይፋ ሥራ ሲያስጀምሩ አንዳሉት ይህ ቦርድ በማንኛውም ጊዜ በሚታወጅ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ  ከሚቋቋም ቦርድ የሚለየው ክቡር ከሆነው የሰው ልጅ ህይወት ጋር በእጅጉ የሚቆራኝ በመሆኑና  የዜጐችን ህይወት ከዚህ አስከፊ ወረርሽኝ ለመታደግ በሚደረገው ርብርብ የተቋቋመ በመሆኑ ታሪካዊ  እንደሚያደርገው ገልፀው፣ ቦርዱ ይህን በመረዳት በከፍተኛ ሃላፊነትና ቁርጠኝነት ኃላፊነቱን ሊወጣ እንደሚገባ አስገንዝበዋል፡፡

የቦርዱ ሰብሳቢ አቶ ዸጥሮስ ወ/ሰንበት በበኩላቸው በዋናነት ቫይረሱ አዲስ ከመሆኑ ጋር ተያይዞ ተለዋዋጭነት ባህሪ ስላለው የቦርዱን ሥራ ተለዋዋጭ ሊያደርገው አንደሚችል ታሣቢ በማድረግ የቦርዱ አባላት ቀዳሚ በመሆን ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ጋር የተለያዮ የመገኛ ቴክኖሎጂዎችን በመጠቀም ፈጣን የሆነ የመረጃ ልውውጥ ማድረግ እንደሚገባ ጠቁመዋል፡፡

ቦርዱ የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ መድሃኒት ያልተገኘለት አደገኛ ወረርሽኝ በመሆኑ በመከላከልና በመቆጣጠር እንዲሁም  የሚያስከትለውን ኢኮኖሚያዊ፣ ማህበራዊና ፖለቲካዊ ቀውስ  ለመቀነስ የታወጀውን አዋጅ ዝርዝር አፈፃፀም ደንብ አተገባበሩን የሚከታተል የሚቆጣጠርና እንደአስፈላጊነቱ የማስተካከያ ሃሳቦችን ለባለድርሻ አካላት በማቅረብ ተፈፃሚ እንዲሆን ያደርጋልም ብለዋል፡፡

በተጨማሪም የአዋጁን ዝርዝር አፈፃፀም ደንብ ከህገ መንግስቱ አንፃር ክለከላ የተደረገባቸውን መብቶች ተገቢነታቸውን በጥልቅ በመመርመር ተፈፃሚነታቸውንም መከታተል እንደሚገባም ጠቁመዋል፡፡

ቦርዱ የአዋጁን አፈፃፀም ለመከታተል ይረዳው ዘንድ የአፈፃፀም እቅድ ያዘጋጀ ሲሆን በእቅዱ የነፃ የሥልክ ጥሪ ማአከል፣ የማህበራዊ ሚዲያ ገጾችን በመክፈት  እና ርቀትን ጠብቆ በሚደረግ የገጽ ለገጽ  ምልከታ  የወረርሽኙ ስርጭት ያለበትን ደረጃ ከህብረተሰቡ ጋር መረጃ መለዋወጥ የሚችልበትን መንገድ አመላክቷል፡፡ የቦርዱ አባላትም የተሰጣቸውን ይህን ታሪካዊ ኃለፊነት በብቃት ለመወጣት ዝግጁ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡