null The compensation for development activists should be set up to permanently establish citizens.

ለልማት ተነሽዎች የሚከፈለው ካሳ ዜጎችን በዘላቂነት ሊያቋቁም የሚችል መሆን እንዳለበት ተገለጸ፡፡

የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በ4ኛ ዓመት የስራ ዘመኑ ባካሄደው 2ኛ አስቸኳይ ስብሰባ የጉምሩክ አዋጅን ለማሻሻል የቀረበውን ረቂቅ አዋጅ፣ እንዲሁም ለህዝብ ጥቅም ሲባል የመሬት ይዞታ የሚለቀቅበትን እና ካሳ የሚከፈልበትን ሁኔታ ለመወሰን የወጣውን ረቂቅ አዋጅ በተመለከተ የቀረቡ ሪፖርቶችንና የውሳኔ ሀሳቦችን መርምሮ አፅድቋል፡፡

የጉምሩክ ማሻሻያ ረቂቅ አዋጁ ለአሰራር እንቅፋት ሆነው የቆዩ ችግሮችን በማስወገድ አዲሱን የጉምሩክ አስተዳደር ስርዓትን ቀላል፣ ቀልጣፋና የተገልጋዮችን ጊዜ የሚቆጥብ እና በቀረጥ ነጻ መብት ስም የሚፈጸሙ የኢኮኖሚ አሻጥሮችን በር ለመዝጋት የሚያግዝ መሆኑ በሪፖርቱ ተጠቅሷል፡፡

በገቢና ወጪ እቃዎች ላይም በመጓጓዣ ሂደት ሲደርስ የነበረውን ቅሸባና መሰል ተግዳሮቶችን ለመቀነስ ሲባል የጭነት ተሽከርካሪዎች ጭነት መቆጣጠሪያ ካርጎ ትራኪንግ እንዲገጥሙ በማድረግ እና ዘርፉን በዘመናዊ ቴክኖሎጂ ለመቆጣጠር የሚያስችሉ አሰራሮች በማሻሻያ ረቂቅ አዋጁ መካተታቸው ተብራርቷል፡፡

በረቂቅ አዋጁ ላይ የጉምሩክ ስነ-ስርዓት የተፈጸመበት ዕቃ በሁለት የስራ ቀናት ውስጥ ከመጋዘን ያልወጣ እንደሆነ አስመጪው 3ሺህ ብር መቀጫ ከፍሎ ዕቃውን ከመጋዘን ይወስዳል የሚለው ቀኑ አንሷል ሲሉ የምክር ቤት አባላት አስተያየት ሰጥተዋል፡፡

የጉምሩክ አዋጅን ለማሻሻል በቀረበው ሪፖርትና የውሳኔ ሀሳብ ላይ ምክር ቤቱ በዝርዝር ከተወያየበት በኋላ አዋጅ ቁጥር 1160/2011 አድርጎ በሙሉ ድምጽ አፅድቆታል፡፡

በተመሳሳይም ለህዝብ ጥቅም ሲባል የመሬት ይዞታ የሚለቀቅበትን እና ካሳ የሚከፈልበትን ሁኔታ ለመወሰን በቀረበው የማሻሻያ ረቂቅ አዋጅን በሚመለከት በከተማም ሆነ በገጠር  ባለይዞታዎች ለህዝብ ጥቅም መሬት እንዲለቁ ሲደረግ በህገ-መንግስቱ የተቀመጡ የመብት ድንጋጌዎችን ያከበረ እና በዘርፉም የመልካም አስተዳደር ስርዓትን በዘላቂነት ለማስፈን የሚደረገውን ርብርብ የሚደግፍ እንዲሁም የመንግስትን ልማታዊነት ለማረጋገጥ የሚያስችል እንደሆነ ነው የተገለጸው፡፡

የልማት ተነሺዎች በዘላቂነት መልሶ ለማቋቋም የሚያስፈልገውን በጀት እንዲሁም በጀቱ በማን እንደሚሸፈን የሚወስነውን አካል ረቂቅ አዋጁ በግልጽ ያመላከተ ሲሆን በሌላ በኩል ለልማት ተነሺዎች ፈንድ መቋቋም እንዳለበት አስገዳጅ ድንጋጌዎችን ያካተተ እንደሆነም ተብራርቷል፡፡

የምክር ቤት አባላት በበኩላቸው የልማት ተነሺዎች የካሳና ተያያዥ ቅሬታቸውን ማቅረብ ሲፈልጉ ቅድሚያ መሬት አስረክበው በፍርድ ቤት እንዲከራከሩ መደረጉ ዴሞክራሲያዊ መብታቸውን የጣሰና የነፈገ መሆኑን ገልጸው ካሁን በፊት የተከሰቱ ችግሮች እንዳይደገሙ በትኩረት መታየት እንዳለበት አሳስበዋል፡፡

በመጨረሻም ም/ቤቱ ለህዝብ ጥቅም ሲባል የመሬት ይዞታ የሚለቀቅበትን እና ካሳ የሚከፈልበትን ሁኔታ ለመወሰን የቀረበውን ረቂቅ አዋጅ አስመልክቶ በቀረበው ሪፖርትና የውሳኔ ሀሳብ ላይ በስፋት ተወያይቶ አዋጅ ቁጥር 1161/2011 ሆኖ በ5 ተቃውሞ እና በ5 ድምጽ ተአቅቦ በአብላጫ ድምጽ ፀድቋል፡፡