null The EBC should avoid the problems of good governance and support reforms in the country.

የኢትዮጵያ ብሮድካስት ኮርፖሬሽን የተጀመረውን ለውጥ ለማስቀጠል በተቋሙ የሚስተዋሉ የመልካም አስተዳደር ችግሮችን በተገቢው መንገድ መፍታት እንዳለበት ተጠቆመ፡፡

ጥር 22 ቀን 2011 ዓ.ም የኢፌዴሪ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የህግ፣ ፍትህና ዲሞክራሲ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ የኢትዮጵያ ብሮድካስት ኮርፖሬሽን የ2011 በጀት አመት የ6 ወር እቅድ አፈጻጸም ሪፖርትን ገምግሟል፡፡

የኮርፖሬሽኑ ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ ስዩም መኮንን ተቋሙ ያከናወነውን የይዘት እና የአቀራረብ ለውጥ ለመተግበር እንዲረዳው የመዋቅር ማሻሻያ በማከናወን እና የሰው ሃይሉን ፍላጎትን መሰረት ባደረገ መልኩ በየሚዲየሞቹ የመመደብ ሥራ አጠናቅቆ በመጀመሪያው ግማሽ ዓመት በኢቲቪ ዜና ቻናል፣ ኢተቪ መዝናኛና ስፖርት፣ ኢቲቪ ቋንቋዎች ቻናል  እና ኢቲቪ ስፖርት ቻናል  እንዲሁም በሬዲዮ በ3 ሚዲየም በሙሉ ሃይሉ ወደ ሥራ እንዲገባ መደረጉን በሪፖርቱ ገልጸዋል፡፡

ከዚህ በተጨማሪም በዲጂታል ሚዲያ ከአሁን በፊት ከነበረው እጅግ በተሻለ አቅም ወደስራ መግባት መቻሉን ጠቁመው፤ ባለፉት ስድስት ወራት የተቋሙ ቁልፍ የትኩረት አቅጣጫ የነበረው የተቋሙን አመራርና ሠራተኛ የማስፈፀም አቅም መገንባት እንደነበርና የተለያዩ የአቅም ግንባታ ስራዎች ማከናወናቸውን አብራርተዋል፡፡

በተቋሙ ሲነሱ የነበሩ የመልካም አስተዳደር ጉዳዮችን መፍታትና በሥራ ሂደት በአዲስ መልክ የሚነሱ ጥያቄዎችን መመለስ እንዲቻል ሠራተኛውን የሚያሳትፍና ችግሮችን ለመለየት የሚረዳ አሠራር ለመዘርጋትና ለመተግበርም ትኩረት ተሰጥቶ እንቅስቃሴ መደረጉን፣ ለስርጭት ጥራት ማሻሻያ ስራዎች መከናወናቸውን በዋናነት አንስተዋል፡፡

ቋሚ ኮሚቴው የተቋሙን አፈጻጸም የተሻለ ለማድረግ የተሰጡ የአቅም ግንባታዎች፣ በይዘትና በአቀራረብ ላይ የታዩ ለውጦች እና ለሰራተኞች በተለይ ለሴቶች ምቹ የስራ ቦታ የመፍጠር ስራዎችን በጥንካሬ አንስቷል፡፡

በሌላ በኩል የተጀመሩ ለውጦችን ለማስቀጠል በተቋሙ የሚስተዋሉ የመለካም አስተዳደር ችግሮችን በተገቢው መንገድ መፍታት እንዳለበት ጠቁሟል፡፡ በተቋሙ ብዝሃነትን የጠበቀ የአመራር ስብጥር እንዲኖር ለማድረግ አሰራሩን መፈተሽ፣ የስነ-ምግባር መመሪያን ተከትሎ መስራትና ተጠያቂነትን ማስፈን እንዳለበት ቋሚ ኮሚቴው አንስቷል፡፡

የቴሌቪዥን ባለይዞታዎችና ባለንብረቶች ክፍያ መሰብሰብ አፈጻጸም ዝቅተኛ በመሆኑ ትኩረት ሊሰጠው እንደሚገባና ዘመናዊ የሆነ የክፍያ ስርአት መዘርጋት እንዳለበት ገልጿል፡፡

በየቅርንጫፉ ያሉ ማሰራጫዎች ላ ክትትልና ድጋፍ ማድረግ፣ በሰራተኛውና በአመራሩ መካከል ያለው ክፍተት ትኩረት ተሰጥቶ ሊሰራበትና ሊስተካከል እንደሚገባ አሳስቧል፡፡

ከቋሚ ኮሚቴው ለተነሱ ጥያቄዎች የተቋሙ ዋና ስራ አስፈጻሚና ሌሎች የስራ ሃላፊዎች ምላሽ ሰጥተዋል፤ አስተያየቶችንም ተቀብለው በቀጣይ እንደሚያስተካክሉም ተናግረዋል፡፡