null The Education and training road map presented to ensure the country middle income goals.

የአገሪቱን የመካከለኛ ገቢ ራዕይ ለማሳካት የሚያስፈልገውን ብቁ የሰው ሃይል በብቃትና በብዛት ለማፍራት የሚያስችል የትምህርትና ስልጠና ፍኖተ ካርታ መዘጋጀቱ ተገለፀ፡፡

የኢፌዴሪ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በትምህርት ፍኖተ ካርታ ረቂቅ ላይ ከትምህርት ሚኒስቴር ጋር ውይይት አካሂዷል፡፡

ውይይቱ ያተኮረው በረቂቁ ላይ በተነሱ የተለያዩ ችግሮችና በቀረቡ ምክረ ሃሳቦች ላይ ሲሆን፣ የትምህርት ሚኒስትሩ ዶ/ር ጥላዬ ጌቴ በጥናቱ የታዩ ችግሮችን በዝርዝር አቅርበዋል፡፡

እየተዘጋጀ ያለው የትምህርትና ስልጠና ፍኖተ ካርታ የአገራችን የመካከለኛ ገቢ ራዕይ ለማሳካት የሚያስፈልገውን ብቁ የሰው ሃይል በብቃትና በብዛት በማፍራት የአገሪቱን ሁለንተናዊ ልማት እና የዴሞክራሲ ግንባታ ስራዎች መደገፍ እንዲቻል ከአለም አቀፍ ስምምነቶች ጋር በማስተሳሰር የሚዘጋጅ ዝርዝር ዕቅድ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

በጥናቱም ከተነሱ ችግሮች ትኩረት የተነፈገውና በአግባቡ ያልተተገበረ የቅድመ መደበኛ ትምህርት፣ ፍትሃዊነትን ሙሉ በሙሉ ያላረጋገጠ የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት፣ የትምህርት ጥራትን ማረጋገጥ ያልቻለ የመምህራን ምልመላና ዝግጅት፣ ፍትሃዊነትና ተደራሽነትን ያላረጋገጠ የቴክኒክና ሙያ ትምህርት ስልጠና እንዲሁም ከኢንዱስትሪው ፍላጎት ጋር ያልተሳሰረ የሙያ ደረጃ ምደባ፣ ፈጠራን የማያበረታታና ከስራ ጋር ያልተቀናጀ ትምህርት የሚኑሱትን በዝርዝር አብራርተዋል፡፡

በተጨማሪም ብቁ ምሩቃን ማፍራት የተሳነው የከፍተኛ ትምህርት ስርአተ ትምህርት፣ የትምህርት ጥራትን ያላረጋገጠ ገንዘብ መሰብሰብ ላይ ያተኮረ የግል ተቋም ሚና፣ በትምህርትና ስልጠና ያሉ ዘርፎችና ባለድርሻ አካላት ተቀናጅቶና ተናቦ አለመስራት የሚሉትን ችግሮች አንስተዋል፡፡

በትምህርትና ስልጠና የሚያስልፈው ትውልድ ከትምህርትና ስልጠናው እውቀት፣ ክህሎትና አመለካከት በበቂ ሁኔታ ይዞ ከመገኘት ይልቅ የምስክር ወረቀት (ዲፕሎማ) አምላኪ መሆኑንና በሂደቱም የኩረጃና የኪራይ ሰብሳቢነት አመለካከት ተግባር ጎልቶ የሚታይ እንደሆነ ለውይይት በቀረበው ረቂቅ ተገልጿል፡፡

በመቀጠልም የትምህርት ሚኒስትር ሚኒስቴር ዴኤታ አቶ መሃመድ አህመዲን በጥናቱ የቀረቡ ምክረ ሃሳቦችን አቅርበዋል፤ ከምክረ ሃሳቦቹ መካከል ዜጎች በራሳቸው የሚተማመኑ፣ ብቁና ምክንያታዊ ትንተናና በውይይት የሚያምኑ በሙያቸው ብቃት ያላቸው በአለም አቀፍ ተወዳዳሪና ብቁ ዜጋ አድርጎ አጠቃላይ ሰብእናቸውን መገንባት እና ቅድመ መደበኛ ትምህርት ህጻናት ከአራት እስከ አምስት ባለው እድሚያቸው እንዲማሩ ማድረግ፣ በመምህራን ትምህርት ላይ ትኩረት አድርጎ የሚሰራ ዩኒቨርሲቲ ማቋቋም፣ ጥራት ያለውና ፍትሃዊ የቴክኒክና ሙያ ትምህርትና ስልጠና ለማዳረስ ሰልጣኞች እያደሩ የሚሰለጥኑበት የቴክኒክና ሙያ ትምህርትና ስልጠና ኮሌጆችና ፖሊቴክኒኮችን ማቋቋም የሚሉት ይገኙበታል፡፡

በአጠቃላይ ትምህርቱን ተጨባጭ የማድረግና ከንድፈ ሃሳብ ይልቅ ተግባር ላይ ያተኮረና ችግር ፈቺ መሆን እንዳለበት አንስተዋል፡፡

ከምክር ቤቱም የተለያዩ ጥያቄዎችና አስተያየቶች የተነሱ ሲሆን የቅድመ መደበኛ ትምህርት ግዴታ መሆን አለበት የሚለው በጥሩ ጎን ተነስቷል፤ ጥናቱ ስራ ላይ ከመዋሉ በፊት በደንብ መታየት እንዳለበት እና ለትምህርት ጥራት ፍትሃዊነትና ተደራሽነት ቅድሚያ መሰጠት እንዳለበትም ተነስቷል፡፡

ለተነሱ አስተያየቶችና ጥያቄዎች የትምህርት ሚኒስትር ሚንስትር ዶ/ር ጥላዬ ጌቴ እና የትምህርት ሚኒስቴር ሚኒስትር ዴኤታ አቶ መሃመድ አህመዲን ምላሽ ሰጥተዋል፤ የቀረበው ረቂቅ ያለቀለት ስላልሆነ ተጨማሪ ሃሳቦችን አደራጅቶ በጽሁፍ ማቅረብ እንደሚቻል ገልጸዋል፡፡