null The Ethiopian Industry Input Organization should focus on domestic products.

የኢትዮጵያ ኢንዱስትሪ ግብአቶች ልማት ድርጅት በገቢ ንግድ ላይ የሚታየውን ጫና ለመቀነስ በሀገር ውስጥ ተኪ ምርቶች ላይ አትኩሮ መስራት እንዳለበት ተገለጸ፡፡

የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የንግድና ኢንዱስትሪ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ የድርጅቱን የ1ኛ ሩብ አመት የእቅድ ክንውን ገምግሟል።

የድርጅቱን የእቅድ አፈጻጸም ሪፖርት ለቋሚ ኮሚቴው ያቀረቡት ዋና ስራ አስፈጻሚው አቶ ወንዳለ ሀብታሙ ሲሆኑ በእቅድ ከተያዙት ተግባራት ውስጥ ለኢንዱስትሪ ግብአት የሚሆኑ ተኪ ምርቶችን ገዝቶ ለገበያ ተደራሽ ማድረግ፣ በዱቤ የተሰጡ ግብአቶችን ገንዝብ የማስመለስና መመለስ ያልቻሉትን በህግ እንዲመልሱ የማድረግ፣ ለኢንዱስትሪ የሚሆን ኬሚካል ግዥ አለም አቀፍ ጨረታ በማውጣት አሽናፊውን መለየት የተከናወኑት ዋና ዋና ተግባራት መሆናቸውን ገልጸዋል።

የድርጅቱ ሀብትና ንብረት የኦዲት ስራ ባለመጠናቀቁና ሂሳቡም ወቅታዊ ባለመሆኑ ድርጅቱ ከባንክ እንዳይበደር ማድረጉንና በዱቤ የተሰጡ ገንዘቦች አለመመለሳቸው በተግዳሮትነት አንስተው ድርጅቱ እንዲጠናከር የቋሚ ኮሚቴው እገዛም እንደሚያስፈልግ ተናግረዋል።

ቋሚ ኮሚቴው ሪፖርቱን ካዳምጠ በኋላ የዱቤ አመላለሱ ሂደት ለምን ዘግየ? መጓተቱስ ለሀብት ብክነት አይዳርግም ወይ? በእቅዱ ዝቅተኛ አፈጻጸም በታየባቸው ጉዳዮች ላይ ከሌሎች ባለድርሻ አካላት ጋር በቅንጅት በመስራት ችግሮቹን ለምን መፍታት አልተቻለም? የሚሉትን በዋናነት ጠይቋል።

የድርጅቱ የስራ ሃላፊዎች በበኩላቸው ድርጅቱ በዱቤ የሰጠውን ገንዘብ በድርድር ማስመለሱን፣ ለመመለስ ፍቃደኛ ያልሆኑትን በህግ በመጠየቅ እንዲመልሱ መደረጉን፣ በክስ ሂደት ያሉትንም ድርጅቱ በማሸነፍ እንደሚያስመልስ፣ ቅንጅታዊ አሰራርን በተመለከተ ችግሩ መኖሩን አምነው በቀጣይ ችግሮችን የመለየት፣ በችግሮቹ ላይ በጋራ መስማማትና በቅንጅት ለመስራት የሚያስችል ሰንድ በመፈራረም ወደ ስራ እንደሚግባ ምላሽ ሰጥተዋል።

በመጨረሻም የቋሚ ኮሚቴው ሰብሳቢ የተክበሩ አቶ ጌታቸው መለሰ ድርጅቱ የራሱን ህንጻ በራሱ ሰራተኞች በማስጠገን ጥቅም ላይ ማዋሉ በርካታ የመንግስትን ገንዝብን ከማዳኑም ባሻገር ለሌሎች ተቋማት አርኣያ ሊሆን መቻሉን፣ የገቢ ንግድና ተኪ ምርቶች እንዲሁም የታጠበ ጨው ግዥን በጥሩ አፈጻጸም አንስተዋል።

በሌላ በኩል የሀገር ውስጥ ተኪ ምርቶች ተገዝተው ካልተሽጡ አሁንም ከውጭ ምርቱ እየግባና በሀገሪቱ ኢኮኖሚ ላይ ጫና የሚፈጥር በመሆኑ ያለው አፈጻጸም በቀጣይ ትኩረት ሊሰጠው እንደሚገባ፣ የዱቤ ሽያጮችን መፈተሽና ገንዘቡ የሚመለስበትን መንገድ ማመቻችት፣ የካይዘን ስራ አመራርን ቅድሚያ ሰጥቶ መተግበር፣ እቅዶች ከአፈጻጸም ጋር ተነጻጽረው መቅረብ እንዳለባቸው እንዲሁም ከዋና ኦዲተር ጋር ተነጋግሮ የሂሳብ ኦዲት ሪፖርትን በማጠናቀቅ ንብረቶቹ ''ራይት ኦፍ'' እንዲደረጉ ሁኔታዎችን ማመቻቸት እንደሚገባ ኣሳስበዋል።