null The Federal Government Budget of 2019 is prepared on the macroeconomic and financial framework.

የ2012 የፌዴራል መንግስት በጀት የማክሮ ኢኮኖሚና የፊሲካል ማዕቀፍ ላይ ተመስርቶ እንደተዘጋጀ ተገለጸ፡፡

ሐምሌ 01 ቀን 2011 ዓ.ም ፤ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በአራተኛ አመት የስራ ዘመኑ ባካሄደው አንደኛ አስቸኳይ ስብሰባ የ2012 በጀት አመት የፌደራል መንግስት በጀት ብር 386,954,965,289/ ሶስት መቶ ሰማንያ ስድስት ቢሊዮን ዘጠኝ መቶ ሃምሳ አራት ሚሊዮን ዘጠኝ መቶ ስልሳ አምስት ሽህ ሁለት መቶ ሰማንያ ዘጠኝ ብር ሆኖ ምክር ቤቱ በሙሉ ድምጽ አጽድቆታል፡፡

በጀቱ የ 2011 በጀት አመት የወጪ አፈጻጸም ሂደትን በመገምገም የማክሮና የፊሲካል ፖሊሲ አላማን ያገናዘበና ራስን የመቻል አቅጣጫን የተከተለ አዘገጃጀት እንደሆነ ተገልጿል፡፡

ድህነት ተኮር ለሆኑ ትኩረት የሰጠ ፤ቁልፍ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ አቅጣጫዎችንና አላማዎችን ለማሳካት ታስቦ የተዘጋጀ በጀት እንደሆነም ተጠቅሷል፡፡

ከአጠቃላይ የፌዴራል መንግስት መደበኛና ካፒታል ወጪ 63 ነጥብ 3 በመቶ የሚሆነው ለትምህርት ፣ ለመንገድ ፣ ለግብርና ፣ ለውሃ ፣ ለጤና እና ለከተማ ልማት እንደተደለደለ ተገልጿል፡፡

የካፒታል ወጪ 34 በመቶ ፣ የክልሎች ድጋፍ ደግሞ 36 በመቶ ሲሆን፤ ከአጠቃላይ ከጸደቀው በጀት ከፍተኛውን ድርሻ እንደያዙ ተጠቅሷል፡፡

የካፒታል ወጪው በመገንባት  ላይ ላሉ ነባር ፕሮጀክቶች ቅድሚያ በመስጠት ይከናወናል ተብሏል፡፡

የምክር ቤቱ አባላት የ 2012 በጀት አመት   የፌዴራል መንግስት በጀትን   አስመልክተው ከመሰረተ ልማት ዝርጋት፤ ስራ አጥነት ፤ ከዋጋ ግሽፈትና ሃብት አጠቃቀም ጋር ተያይዞ   የሚስተዋሉ ችግሮችን ለመቅረፍ ጥያቄዎቻቸውን ለጠቅላይ ሚኒስትሩ አንስተዋል፡፡

የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ  ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ.ር ዐቢይ አህመድ  በምክር ቤቱ በመገኘት  ከምክር ቤት አባላት  ለተነሱላቸው ጥያቄዎች ማብራሪያና ምላሽ ሰጥተዋል፡፡

በምላሻቸውም የዋጋ ግሽፈቱን ለመቀነስ በፍላጎትና አቅርቦት መካከል ያለውን ክፈተት ለመሸፈን አቅርቦት ላይ ያተኮረ ስራ እንሰራለን ብለዋል፡፡

ለግሽፈቱ ምክንያት የሆኑ ሰው ሰራሽ ክምችቶችን ፣ የመብራት አቅርቦት እጥረት ፣ የሎጅስቲክስ መጓተት ፣ የወደብ ላይ ክምችት ፣ የንግድ ስርዓት አሰራር ፣ ምክንያታዊ ያልሆነ የቤት ኪራ ጭማሪ  ላይ የሚስተዋሉ ችግሮችን ለመፍታት  በጥናት ላይ  የተመሰረተ አሰራር እንደሚኖር ዶ.ር ዐቢይ ተናግረዋል፡፡

የዋጋ ግሽፈቱን ለመቆጣጠር የተቋቋመው ኮሚቴ  የራሱን አዎንታዊ አስተዋጽኦ እንደሚያደርግም  ዶ.ር ዐቢይ ጠቅሰዋል፡፡

በቀን አንዴ ለመመገብ ለተቸገሩ የድሃ ድሃ የህብረተሰብ ክፍሎችን ችግር ለመቅረፍ  በቀን በርካታ ሚሊዮን ዳቦ መጋገር የሚችል የዳቦ ፋብሪካ በ2012 ዓ.ም ለመገንባት እንደታሰበም ጠቅላይ ሚኒስትሩ ገልጸዋል፡፡

የወጣቶችን የስራ አጥነት ቁጥር ለመቀነስ መንግስት በዚህ አመት ሶስት ሚሊዮን ወጣቶች የስራ እድል እንዲያገኙ ማቀዱን ገልጸዋል፡፡

 በርካታ ወጣቶችን  በልዩ ልዩ የስራ ዘርፎች አሰልጥኖ  ወደ ውጭ በመላክና የስራ አጥነት ቁጥሩን ለመቀነስ ከተለያዩ የመካከለኛው ምስራቅ ፣ የአውሮፓና ሩቅ ምስራቅ  ሃገራት ጋር ድርድር እየተደረገ እንደሚገኝም ጠቅሰዋል፡፡

 በተደረገው ድርድርም በ 2012 በጀት አመት 50,000 /ሃምሳ ሽህ / ስራ ፈላጊዎች በተለያዩ የስራ መስኮች ሰልጥነው ወደ ዱባይ እንደሚሄዱ ዶ.ር ዐቢይ ተናግረዋል፡፡

በሃገር ውስጥ ስራ ፈጠራ ፣ በግብርና ፣ በኢንዱስትሪዎች ፣ በማዕድናትና በ2012 በጀት አመት ሊሰሩ በታቀዱ ልዩ ልዩ ፕሮጀክቶች ላይ ወጣቶች እንደሚሰማሩም አክለዋል፡፡

የስራ አጥነት ቁጥር ለመቀነስ ባላሃብቶችና የመንግስት ሹማምንቶች በጋራ ሆነው እንዲሰሩም ጥሪያቸውን አቅርበዋል፡፡

ከመንገድ መሰረተ ልማት ጋር ተያይዞ ለቀረበላቸው ጥያቄም ማብራሪያ የሰጡ ሲሆን፤ ተጀምረው የነበሩ የመንገድ ፕሮጀክቶች በ 2012 በጀት አመት እንደሚገነቡና ለግንባታውም ለትምህርት ከሚወጣው ወጪ ቀጥሎ የተያዘ በጀት እንደሆነ ዶ.ር ዐቢይ ገልጸዋል፡፡

የሃብት አጠቃቀምን አስመልክቶ ለተነሳላቸው ጥያቄም ምላሽ የሰጡ ሲሆን፣  ወጪ ቅነሳን መሰረት ያደረገ የሃብት አጠቃቀም ከባለፈው አመት ጀምሮ ተግባራዊ እየተደረገ መምጣጡን አውስተው ፤ ይሄ አሰራርም በዚህ በጀት አመት በተሻለ መንገድ ተጠናክሮ እንደሚቀጥልም ጠቅሰዋል፡፡

ተጨማሪ ገቢ ለመሰብሰብ  በርካታ  ገቢ ማስገኘት የሚችሉ ያልታዩ ሀብቶች እንዳሉጠቅላይ ሚኒስትሩ  ተናግረዋል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር እና የኢፌዴሪ ፕሬዚዳንት አንድ ግቢ ውስጥ እንዲኖሩና የታችኛው ብሄራዊ ቤተ መንግስት ለጎብኝዎች ክፍት እንዲደረግ እየተሰራ እንደሆነ  ዶ.ር ዐቢይ ገለጸዋል፡፡