null The Food and Medicine administration has been facing a number of bottlenecks since the proclamation number 661/2009 ratified.

የምግብና መድሃኒት አስተዳደር አዋጅ ከአቀራረጹ ጀምሮ እስከ ተግባራዊነቱ በርካታ ክፍተቶች የታዩበት በመሆኑ አዋጁን ማሻሻል እደሚገባ ተገለፀ፡፡ 

የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ታህሳስ 2/2011 ዓ.ም ባካሄደው መደበኛ ስብሰባ የምግብ እና መድሃኒት አስተዳደር እና የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ጽ/ቤትን ለማቋቋም በቀረቡ ረቂቅ የማሻሻያ አዋጆች ላይ ውይይት አድርጓል፡፡

የምግብና መድሃኒት አስተዳደር አዋጅ ቁጥር 661/2002 በፌደራልና በክልል መንግስታት ተለይተው ሊሰሩ የሚገባቸው የምግብ፣ መድሃኒት፣ የጤና ተቋማት ወዘተ ስራዎች እንዲሰሩ በተሰጠው ስልጣንና ሃላፊነት መሰረት ላለፉት ስምንት አመታት በርካታ ስራዎች ሲሰሩ መቆየታቸውን የመንግስት ረዳት ተጠሪ ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ጫላ ለሚ አውስተዋል፡፡

ይሁን እንጂ አዋጁ ከህግ አቀራረጹ ጀምሮ እስከ ተግባራዊነቱ በርካታ ክፍተቶች  እንዳሉበት ከባለድርሻ አካላትና ከክልል ጤና ተቆጣጣሪ አካላት ጋር በተካሄዱ ውይይቶችና ጥናቶች  ችግሩን ለመለየት እንደተቻለ አቶ ጫላ አብራርተዋል፡፡

የአዋጁ መሻሻል አስፈላጊነት የሃገሪቱን የጤና ቁጥጥርና ተያያዥ ጉዳዮች ወደተሻለ ደረጃ ከፍ ለማድረግ እንደሆነ አቶ ጫላ ተናገረው፤ ለውጤታማነቱም አስራ አምስት አዳዲስ ድንጋጌዎች መካተታቸውንም አክለው ገልጸዋል፡፡

ከቁጥጥር ስርዓቱ ጋር በተያያዘ የአልኮል መጠጥ ማስታወቂያዎች የትውልድ ግንባታ ሂደት ላይ እንቅፋት እየፈጠሩ ስለሆነ ከምሽቱ 3 እስከ ንጋቱ 12 ሰዓት ማስታወቂያዎቹ  እንዲተላለፉ የሰዓት ገደብ ከመጣል ይልቅ በመጠጥ ማስታወቂያዎቹ ይዘቶች ላይ  ትኩረት ተደርጎ ቢሰራ፣ የመንግስት ሚዲያው ሳይቀር የማስታዎቂያ ሽፋን እየሰጠ  እንደሚገኝም የምክር ቤት አባላቱ አስተያየታቸውን ሰንዝረዋል፡፡

የአልኮል መጠጥ ማስታወቂያዎቹ ህጻናትን ሳይቀር ለመጠጥ የሚገፋፉ ይዘቶችን አካተው ስለሚተላለፉ ይዘታቸው ላይ መንግስት በአጽእኖት እንዲያየው አስተያየታቸውን ገልጸዋል፡፡

ረቂቅ አዋጁ ከምክር ቤት አባላት የተነሱ አስተያየቶችን አካቶ ለዝርዝር እይታ በዋናነት ለሴቶች፣ ወጣቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ቋሚ ኮሚቴ በተባባሪነት ለንግድና ኢንዱስትሪ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ተመርቷል፡፡

በሌላ ዜና ም/ቤቱ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ጽ/ቤትን ማቋቋሚያ አዋጅ ለማሻሻ የቀረበለትን  ረቂቅ አዋጅ ተመልክቷል፡፡

የፅ/ቤቱን ማሻሻያ ረቂቅ አዋጅ ማብራሪያ ያቀረቡት የምክር ቤቱ አፈ-ጉባኤ አቶ ታገሰ ጫፎ ሲሆኑ፤ የምክር ቤት ጽ/ቤቱን ለማሻሻል የቀረበው ረቂቅ አዋጅ አስፈላጊነት በዋናነት ምክር ቤቱ የጀመረውን የለውጥ ስራዎች ብቃት ባለው የሰው ሃይል ለመምራትና ለመደገፍ  እንዲያስችል ታስቦ መሆኑን አብራርተዋል፡፡

የም/ቤት አባላቱም ጽ/ቤቱን እንደገና ለማደራጀት የቀረበው ረቂቅ አዋጅ አስፈላጊ ቢሆንም አደረጃጀቱ በቂ ጥናት ቢደረግበት፣ ከአመራር ጋር በተያየዘ የጽ/ቤቱ ምክትል ዋና ጸሃፊዎች ሶስት እንዲሆኑ የተፈለገበት ምክንያት በአሳማኝ ምክንያት ቢገለጽ የሚሉ ነጥቦችን አንስተዋል፡፡

ምክር ቤቱም ጽ/ቤቱን ለማቋቋም የቀረበለትን ረቂቅ የማሻሻያ አዋጅ ለዝርዝር እይታ ለሰው ሃብትና ቴክኖሎጂ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ መርቶታል፡፡