null The government is making a concerted effort to stabilize living costs and inflation.

የኑሮ ውድነትን እና የዋጋ ንረትን ለማረጋጋት መንግስት ሁለንተናዊ ጥረት እያደረገ እንደሆነ ተገለጸ፡፡

በ5ኛው የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት 5ኛ ዓመት የስራ ዘመን 2ኛ መደበኛ ስብሰባ በአገሪቱ ኢኮኖሚያዊ፣ ማህበራዊ እና ፖለቲካዊ ጉዳዮች ዙሪያ ከምክር ቤት አባላት ለተነሱ ጥያቄዎች ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር አብይ አህመድ ምላሽ ሰጥተዋል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር አብይ አህመድ በአገሪቱ የሚስተዋለውን የኑሮ ውድነትና የዋጋ ንረትን በተመለከተ ከምክር ቤት አባላት ለተነሱላቸው ጥያቄዎች ምላሽ በሰጡበት ወቅት ለህዝቡ አንገብጋቢ ችግር የሆኑት የቤት ችግር፣ የምግብ አቅርቦት፣ ስራ አጥነት እና የምርት መጠኑ ገበያ ላይ ከሚፈለገው ያነሰ መሆን በማሳያነት አንስተዋል፡፡

የኑሮ ውድነቱንም ሆነ የዋጋ ንረቱን ለማረጋጋት መንግስት ሁለንተናዊ ጥረት እያደረገ መሆኑን የገለጹት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ የቤት ችግሩን ለመቀነስ በአዲስ አበባና በክልል ከተሞች በመንግስትና በግል በለሀብቶች የጋራ ትብብር በከፍተኛ ወጪ የቤቶች ግንበታ እንዲካሄድ የተለያዩ ስምምነቶች መፈራረማቸውን ተናግረዋል፡፡

ከ4 እስከ 5 ሺህ የጎዳና ተዳዳሪዎችን ለማንሳት የሚያስችል ቤት ግንባታው እየተካሄድ እንደሆነም ገልጸዋል፡፡

በተመሳሳይም ከምግብ አቅርቦት ችግር ለመላቀቅ ዝቅተኛ ገቢ ያላቸውን የማህበረሰብ ክፍሎች ታሳቢ ያደረገ በቀን እስከ አንድ ሚሊየን ዳቦ ማምረት የሚችል የዳቦ ፋብሪካ መገንባቱን ገልጸው ከአረብ ኢምሬት በተገኘ የገንዘብ ድጋፍ ደግሞ በቀን እስከ 10 ሚሊየን ዳቦ ማምረት የሚችል የዳቦ ፋብሪካ በቀጣይ ግንባታው የሚጠናቀቅ መሆኑን አስረድተዋል፡፡

የከተማ እርሻና የአትክልት ቦታዎችን በማስፋፋት በትንሹም ቢሆን የስራ አጥነትን ችግር ለመቅረፍ ጥረት መድረግ እንዳለበት ያሳሰቡት ጠቅላይ ሚኒስትሩ በተያዘው በጀት አመት የምርት መጠኑ የተሻለ እንደሆነ እና በ3 ወራት ውስጥ የግብርናው ኤክስፖርት አፈጻጸም 101 ፐርሰንት መከናወኑን ጠቁመዋል፡፡

በሌላ በኩል የአገሪቱን የቱሪዝም ዘርፍና ኢኮኖሚያዊ ፋይዳውን አስመልክቶ ከምክር ቤት አባላት ለተነሳው ጥያቄ ዶ/ር አብይ አህመድ ምላሽ በሰጡበት ወቅት ጭስ አልባው ኢንዱስትሪ ቱሪዝም ከአረንጓዴ ልማቱ ጋር የሚሰራ ሲሆን አገሪቱ ከዘርፉ ከፍተኛ ገቢ እንድታገኝ የሚረዳና የውጭ ምንዛሬ ችግር የሚቀርፍ እና ለብዙ ዜጎች ሰፊ የስራ እድል የሚፈጥር እንደሆነ ገልጸዋል፡፡

አገሪቱ የበርካታ ተፈጥሮ ሀብትና ሰው ሰራሽ ባለቤት መሆኗን የገለጹት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ በአዲስ አበባና በክልሎች የሚገኙ ቅርሶች እንዲጎበኙ በቀጣይ ሰፊ ስራ ለመስራት እንደታሰበ ተናግረዋል፡፡

በታላቁ ቤተ-መንግስት የሚገኘው አንድነት ፓርክ ባለፉት ስድስት ወራት ውስጥ ግንባታው ተጠናቆ በቀን በሺዎች የሚቆጠሩ ዜጎች እየጎበኙት እንደሆነም ተናግረዋል፡፡

የአዲስ አበባ አበባ መንገዶችን፣ መዝናኛ ቦታዎችን በማስዋብ እንዲሁም የሆቴሎችን ደረጃ በማሻሻል ከቱሪዝም ዘርፉ ተጠቃሚ ልንሆን ይገባል ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትሩ አብራርተዋል፡፡