null The House confirmed that the Nech-sar National park is in dangerous situation and the regional state said the problem is beyond its capacity.

ነጭ - ሳር ብሔራዊ ፓርክ ህልውናው አደጋ ውስጥ መሆኑን የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አረጋገጠ፡፡ ክልሉል ችግሩ ከአቅሜ በላይ ነው አለ፡፡

በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት  የሴቶች፣ ወጣቶችና ማህበራዊ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ በደቡብ ብሔር፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት ስላለው የቱርስት ፍሰት፤ የመዳረሻ ቦታዎች ምቹነት፤ የቱርዝም መረጃ አያያዝና አሰጣጥ እና ዘርፉ የፈጠረውን የስራ ዕድል ለመመልከት በነጭ - ሳር ብሔራዊ ፓርክ፣ በአርባ - ምንጭ አዞ ማሳደጊያ ማዕከል እና በአርባ ምንጭ ቱርስት ሆቴል የመስክ ምልከታ ሚያዚያ 6 እና 7 ቀን 2011 ዓ.ም አካሂዷል፡፡

በክልሉ ውስጥ አርባ - ምንጭና አካባቢው  በቱርስት ፍሰት ከሐዋሳ ቀጥሎ በሁለተኛ ደረጃ ላይ የሚገኝ ሲሆን ባለፉት 9 ወራት 150,264 የአገር ውስጥና 35,118 የውጭ አገር ጎበኚዎችን አስተናግዷል፡፡ በየዓመቱ ዘርፉ ለአካባቢው ከ154 ሚሊዮን ብር ገቢ እንደሚያመነጭና በሺዎች ለሚቆጠሩ ዜጎች የስራ ዕድል እንደሚፈጥር ከጋሞ ዞን የባህልና ቱርዝም የስራ ሃላፊዎች ገለፃ ለመረዳት ተችሏል፡፡ ከአርባ - ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ጋር በመተባበርም የቱርስት መረጃ ማዕከል ለመገንባት ከጫፍ እንደተደረሰም እነዚህ የስራ ሃላፊዎች አስረድተዋል፡፡

አርባ - ምንጭ ቱርስት ሆቴልን ጨምሮ ሁለት ባለአንድ ኮከብ ሆቴል ደረጃ ሆቴሎች በአርባ - ምንጭ ከተማ ሲገኙ በ2011 በጀት ዓመት አራት ተጨማሪ ሆቴሎችን ወደኮከብነት ደረጃ ለማሳደግ ዕቅድ ተይዞ እየተሰራ ሲሆን ሃይለ ገብረ ስላሴ ሪሶርት ለባለ አምስት እና ኤሜራልድ ሆቴል ለባለ አራት ኮከብ ደረጃ መታጨታቸውን ለማወቅ ተችሏል፡፡

የቱርስት ፍሰቱን ለመጨመርና ከዘርፉ የሚገኘውን ገቢ ለማሳደግ በአካባቢው ሰፊ እንቅስቃሴ መኖሩን የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት የተገነዘቡ ቢሆንም ለአርባ - ምንጭና ዙሪያው አንዱ የቱርስት መዳረሻ የሆነው ነጭ - ሳር ብሔራዊ ፓርክ ግን ህልውናው ወደማክተም ደረጃ መሸጋገሩ ነው የታየው፡፡ ከፓርኩ ክልል ውስጥ 25 በመቶው በሕገ - ወጥ ሰፈራ ምክንያት ሙሉ በሙሉ ወድሞ ሁለት የጉብኝት ጣቢያዎች መዘጋታቸውን ከፓርኩ ሃላፊ ለመረዳት የተቻለ ሲሆን ሃላፊው ፓርኩ ህግና ስርዓት የማይከበርበት ቀጠና ሆኗል ሲሉም አክለዋል፡፡

ሰፋሪው በቀሪው የፓርኩ ክልል ውስጥ ደግሞ በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ከብቶችን ለግጦሽ በማሰማራት ‘’ነጭ - ሳር’’ የተባለውን የፓርኩን መለያ ሳር አውድሞ ድንጋያማ መሬት ከመቅረቱ ባሻገር የሳሩ ቦታ በመጤ አረሞች ተወርሮ ሜዳ ፍየልና ሜዳ አህያ የማይኖሩበት ስነ ምህዳር መሆኑን ለመመልከት ተችሏል፡፡

አደኑም ተባብሶ ሜዳ ፍየልና አጋዘን በየቀኑ ሲገደሉ የደን ጭፍጨፋውና የእሳት ቃጠሎው የፓርኩን ህልውና በተጨማሪነት እየተፈታተኑ መሆናቸው ታይቷል፡፡ የቡድኑ አስተባባሪ የተከበሩ አቶ ሙላጎ ሻፊ ፓርኩ ኢትዮጵያን በዓለም መድረክ በማስተዋወቅ በኩል የአገር ባንድራ ሆኖ ማገልገሉን አስታውሰው አሁን ፓርኩ ያለበት ሁኔታ በፓርክነት መቀጠሉ ቀርቶ ስያሜውን እንኳን ይዞ መቆየት የማይችልበት ደረጃ መድረሱን በሰጡት አስተያየት አረጋግጠዋል፡፡

የጋሞ ዞን ምክር ቤት አፈ ጉባኤ የተከበሩ ወ/ሮ ልሳነ ወርቅ ካሳዬ የህዘብ ተወካዮች ምክር ቤት ነጭ - ሳር ብሔራዊ ፓርክን ከመጥፋት እንዲታደግ ተማፅነዋል፡፡ የክልሉ መንግስት የዘርፉ ሃላፊዎችም ፓርኩ ውስጥ የሚደረገውን ህገ ወጥ ሰፈራ የክልሉ መንግስት ለመከላከል ቢችልም ከክልሉ መንግስት ስልጣን ክልል ውጭ ባሉ የፓርኩ ክልሎች ውስጥ የሚደረገውን ህገ ወጥ ሰፈራ ለመከላከል ስልጣን ስለሌለ ከ50 በመቶ በላይ የዱር እንስሳቱ መገደላቸውንና ቀላል የማይባል ቁጥር ያላቸው እንስሳት መሸሻቸው የተገለፀ ሲሆን  ፓርኩን የመታደግ ብቸኛ ስልጣን ያለው የፌዴራል መንግስት በመሆኑ ስልጣኑን እንዲወጣ ኮሚቴው የራሱን ሚና እንዲጫወት የክልሉ መንግስት የስራ ሃላፊዎች ጠይቀዋል፡፡