null The House endorsed a bill establishing a reconciliation commission.

ምክር ቤቱ የዕርቀ-ሰላም ኮሚሽንን ለማቋቋም የቀረበለትን ረቂቅ አዋጅ አጸደቀ፡፡

የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ታህሳስ 16/2011 ዓ.ም ባካሄደው 14ኛ መደበኛ ስብሰባ የዕርቀ-ሰላም ኮሚሽንን ለማቋቋም የቀረበውን ረቂቅ አዋጅ በአንድ ተቃውሞ፣ በአንድ ድምፀ ተዐቅቦ እና በአብላጫ ድምጽ አጽድቆታል፡፡

የዕርቀ-ሰላም ኮሚሽኑ ዋና አላማ አገራችን ከገባችበት ፖለቲካዊ፣ ምጣኔ ሃብታዊና ማህበራዊ ችግሮች መሰረታዊ በሆነ መልኩ እንድትወጣ ሃገራዊ እርቅና ይቅርታ ማካሄድ አስፈላጊ መሆኑን የውጭ ግንኙነትና የሰላም ጉዳዮች ሰብሳቢ የተከበሩ አቶ ተስፋዬ ዳባ አብራርተዋል፡፡

ሃገራዊ መግባባት በመፍጠር የቂምና በቀል ስሜቶችን በማስወገድ በህዝቦች መካከል አንድነትን በማጠናከር ሃገሪቱ የጀመረችውን የለውጥ ሂደት ለማሳለጥ የኮሚሽኑ መቋቋም  ሚናው ላቅ ያለ መሆኑን አቶ ተስፋዬ ገልጸዋል፡፡

የሰላም አላማን ያነገበ ለግጭቶችና ቁርሾዎች ምክንያት የሆኑትን ዝንፈቶች የስፋት መጠን አጣርቶ እውነታውን በማውጣት ችግሮቹ ተመልሰው እንዳይከሰቱ በዘላቂነት ለመፍታት የሚያስችልና የመፍትሄ አቅጣጫዎችንም የሚያመላክት እንደሆነም አቶ ተስፋዬ አክለዋል፡፡

የኮሚሽኑ አባላት ገለልተኝነታቸው እስከ ምን ድረስ ነው? እንደ ህዝብ የተጋጨ ህዝብ የለም ዕርቁ የፖለቲካ ድርጅቶች እርቅ ለምን አይሆንም? የሚሉ ጥያቄዎች ከምክር ቤት አባላት ተነስተዋል፡፡

የኮሚሽኑ አባላት ከማንኛውም ተጽዕኖ ገለልተኛ ሆነው ተበድያለው የሚለውን የህብረተሰብ ክፍል እውነታ በማፈላለግና ላለፈው በደል ይቅርታ በማድረግ ለወደፊቱ ደግሞ በአብሮነት ላይ የተመሰረተ ሃገራዊ እሴቶቻችን ተጠናክረው እንዲቀጥሉ የሚያስችል ኮሚሽን መሆኑን አቶ ተስፋዬ ዳባ በምላሻቸው አብራርተዋል፡፡

ዕርቁ የኢትዮጵያ ህዝቦች ጉዳይ ስለሆነና ከፍተኛ ትኩረት ተሰጥቶት ዘላቂ ሰላምና ዋስትና ያለው ዴሞክራሲ እንዲመጣና አሁን የተጀመረውን ለውጥ እንዲያስቀጥል ያለመ መሆኑን አቶ ተስፋዬ አብራርተው፤ ዕርቁ ዝቅ ብሎ በፖለቲካ ድርጅቶች ደረጃ ብቻ የሚከናወን  ጉዳይ እንዳልሆነም ገልጸዋል፡፡  

በመጨረሻም ምክር ቤቱ 14ኛ መደበኛ ጉባኤውን መርምሮ በሙሉ ድምጽ አጽድቆታል፡፡