null The House evaluated 6 months performance report of the Ministry of Health.

በጤና ተቋማት የሚሰጠው የወሊድ አገልግሎት አፈፃፀም ዝቅተኛ መሆኑንና በገጠርም ሆነ በከተማ የጤና ኤክስቴንሽን ፕሮግራም ከጊዜ ወደ ጊዜ መቀዛቀዝ እደሚታይበት ተገለፀ፡፡  

የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የጤና ጥበቃ ሚኒስቴርን የ2011 በጀት ዓመት የ6 ወራት የቅድ አፈፃጸም ሪፖርት ገምግሟል፡፡

በውይይቱም የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር ሚኒስትር ዶ/ር አሚር አማን የጤናው ዘርፍ የአገሪቱ የሁለተኛው ትራንስፎርሜሽን እቅድ አካል ሆኖ የዘላቂ ልማት ግቦችንና የአፈጻጸም መለኪያዎችን ታሳቢ ባደረገ መልኩ ተዘጋጅቶ ወደ ትግበራ ከገባ አራተኛ አመቱን እንደያዘ በሪፖርቱ ገልፀዋል፡፡

አገሪቱ በቀጣይ 20 ዓመታት ውስጥ ከአገሪቱ የጤና ፖሊሲ ጋር የተጣጣሙ የተለያዩ የፖሊሲ አቅጣጫዎችን በመቀየስ ላይ እንደምትገኝ ፖሊሲው በዋናነት የማህበረሰብ ባለቤትነትን ማረጋገጥ፣ ፍትሃዊና ጥራት ያለው የጤና አገልግሎት መስጠት፣ የህብረተሰብ ጤና አደጋዎችንና መሰል ክስተቶችን የሚቋቋምና ፈጣን ምላሽ የሚሰጥ የጤና ስርኣት መዘርጋት፣ የጤናው ዘርፍ የሰው ሀብት ልማት ማሻሻል፣ የጤና መረጃ ጥናትና ምርምርና የእውቀት አስተዳደርን ማጎልበት፣ የጤና ስርዓት አመራርና አስተዳደር ማጠናከርና የባህል ህክምና ማሻሻል ላይ ትኩረት ተደርጎ እንደሚሰራ ነው ለምክር ቤቱ ያብራሩት፡፡

አክለውም በበጀት ዓመቱ የመጀመሪያው 5 ወር ለ4 ሚሊዮን ሰዎች የኤ.ች አ.ቪ ምርመራና ምክር አገልግሎት ለመስጠት ታቅዶ 3 ሚሊዮን የሚሆኑ ተጠቃሚዎች እንደሆኑና ምርመራ ካደረጉት 29,639 የሚሆኑ የአ.ች.አይ.ቪ ቫይረስ በደማቸው የተገኘባቸው ሲሆኑ ከዚህ ቁጥር መካከል 7,167 (24%) የሚሆኑት ይበልጥ ተጋላጭ የሆኑ የህብረተሰብ ክፍሎች እንደሆነም ጠቁመዋል፡፡  

የሴቶች፣ ወጣቶችና ማህበራዊ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ የተከበሩ ወ/ሮ አበባ ዮሱፍ የህጻናት ጤናን ከማሻሻል የሚሰጠውን የክትባት አገልግሎት የተሻለ አፈጻጸም መኖሩ፣ ለመጀመሪያ ጊዜ በሀገራችን የተጀመረውን የማህጸን በር ጫፍ ካንሰር ለመከላከል የሚሰጠው የክትባት ሽፋን የተሸለ መሆኑ፣ የብሄራዊ ህክምና አደጋ ቡድን መቋቋምና ወደ ስራ መግባቱ፣ ለረጅም ጊዜ የቀዶ ህክምና ወረፋ ሲጠብቁ የነበሩ ህመምተኞች 55% መቀነስ መቻሉ፣ ከ500 በላይ የጎዳና ተዳዳሪ ወገኖች ሁለት ጊዜ የጤና ምርመራና ህክምና በመስጠት በቀጣይ መታከም እንዲችሉ መመቻቸቱ እንዲሁም በደም እጦት ምክንያት የሚከሰጠውን ሞት ለመቀነስ በመጀመሪያው ግማሽ ዓመት 71.8% ዩኒት ለመሰብሰብ  የተሰራው ስራ የተሻለ አፈፃጸም እንደሆነና በቀጣይም ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት አንስተዋል፡፡

በሌላ በኩል የጤና ኤክስቴንሽን ፕሮግራም በገጠርም ሆነ በከተማ ከጊዜ ወደ ጊዜ የመቀዛቀዝና በአፈጻጸም ወደ ኋላ የመመለስ አዝማሚያ እንደሚታይ፣ ለእናቶች ሞት እስከ 30% አስተዋጽኦ ያለው የቤተሰብ ምጣኔ አገልግሎት አፈጻጸም እና በሰለጠነ ባለሙያ በጤና ተቋማት የሚሰጠው የወሊድ አገልግሎት ዝቅተኛ መሆኑ፣ ለአብነት በጋምቤላ 63%፣ በአፋር 69% እና በሱማሌ 87% በቤት ውስጥ መውለዳቸውን አንስተዋል፡፡ ስለሆነም አፈጻጸሙ እጅግ ዝቅተኛ በመሆኑ በቀጣይ ልዩ ትኩረት ተደርጎ መሰራት እንዳለበት ነው ሰብሳቢዋ ያስገነዘቡት፡፡ 

አክለውም ቋሚ ኮሚቴው በመስክ ምልከታው እንዳረጋገጠው በጤና ተቋማት መካከል የሚደረገው የሪፈራል ቅብብሎሽ የተጠናከረ አለመሆኑን በተለይም ደግሞ ጤና ጣቢያዎች በሰው ሀይልና በግብዓት አለመሟላት እናቶች አገልግሎቱን በቅርበት እንዳያገኙ እንቅፋት መሆኑን ጠቁመው የሪፈራል አሰራር ስርአቱ መጠናከር እንዳለበት አሳስበዋል፡፡

በተጨማሪም የመድሀኒት፣ የሪኤጀንቶችና አቅርቦትና ተደራሸነት ችግር እንዲሁም የህክምና መሳሪያዎች ተከላና ጥገና ችግሮች በጤና ተቋማት ላይ መስተዋላቸው፣ የፋይናስ አጠቃቀምን ከማሻሻል አኳያ በመጀመሪያው ግማሽ ዓመት የመስሪያ ቤቱ በጀት አጠቃቀም ዝቅተኛ ከመሆኑ በላይ በመደበኛና በካፒታል ዘርፍ ተለይቶ አለመቀመጡንም በእጥረት አንስተዋል፡፡

በመጨረሻም ከቡር ሚኒስትሩ ሪፖርቱን በተመለከተ አጠቃላይ የምክር ቤቱ አባላት ያነሷቸውን ነጥቦች ተገቢነት እንዳላቸው ጠቁመው በቀጣይ ትኩረት ተደርጎባቸው እንደሚሰራ፣ በየቦታው በሚታየው የህገ-ወጥ የመድሀኒት ዝውውር ላይ ም/ቤቱና  መንግስት ሊያግዛቸው እንደሚገባ ገልፀዋል፡፡