null The House has decided that the Addis Ababa and Dire Dawa City elections will be held in accordance with the calendar set by the Board.

ምክር ቤቱ ዛሬ ባካሄደው 2ኛ አስቸኳይ ስብሰባው የአዲስ አበባ እና የድሬዳዋ ከተሞች ምክር ቤቶች እንዲሁም የአካባቢ ምርጫዎችን በብቃት ለማካሄድ የሚያስችሉ ሁኔታዎች ባለመኖራቸው በቦርዱ በሚዘጋጀው ጠቅላላ ምርጫ ካላንደር መሰረት እንዲካሄድ ወሰነ፡፡

የምክር ቤቱ አፈ-ጉባኤ የተከበሩ አቶ ታገሰ ጫፎ ለምክር ቤቱ እንዳስረዱት የሀገራችንን የዲሞክራሲ እና የመድብለ ፓርቲ ስርአት ለማጠናከር የብሄራዊ ምርጫ ቦርድን የህግ ማዕቀፍ፣ የአመራሮች አመራረጥ፣ ዘመናዊ አሰራር መዘርጋት እንዲሁም ተፎካካሪ ፓርቲዎች የጋራ አሰራር እና መድረክ እንዲፈጠርላቸው ማድረግ በሪፎርሙ ትኩረት ተሰጥቷቸው እየተሰሩ ያሉ ስራዎች ናቸው ብለዋል፡፡

በመሆኑም ካለው የጊዜ ማነስ አንጻር የምርጫ አስፈጻሚዎችን መመልመል፣ ማደራጀት፣ ስልጠና መስጠት እና ተቋማዊ የሪፎርም ስራዎችን በክልል አጠናቆ ማስፈጸም ስለማይቻል ምርጫውን በተቀመጠው ጊዜ ማካሄድ እንደማይቻል ቦርዱ ለምክር ቤቱ ያቀረበ መሆኑን አስታውሰው የቦርዱን ውሳኔ ከግንዛቤ በማስገባት ምክር ቤቱ የቀረበውን የውሳኔ ሃሳብ እንዲያፀቀው ባቀረቡት መሰረት ምክር ቤቱም የውሳኔ ሃሳቡን መርምሮ የውሳኔ ሃሳብ ቁጥር 33/2011 አድርጎ አፅድቆታል፡፡

በሌላ በኩል የባንክ ስራ አዋጅን ለማሻሻል የቀረበ ረቂቅ አዋጅን በሚመለከት የባንክ ኢንዱስትሪውን ለማዘመን፣ የፋይናንስ አገልግሎት ተደራሽነትና ቅልጥፍናን ለማጎልበት እንዲሁም ከዚህ ቀደም በስራ ላይ አስቸጋሪ ሆነው ከተገኙት የአዋጅ አንቀጾች እና ንዑስ አንቀጾችን በማሻሻል በአሰራር ላይ ያጋጠሙ ችግሮችን መፍታት እንዲቻል እና ለሚነሱ ቅሬታዎች ምላሽ ለመስጠት የሚረዳ በመሆኑ የገቢዎች በጀት እና ፋይናንስ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ አዋጁን አስመልክቶ ያዘጋጀውን ሪፖርትና የውሳኔ ሀሳብ ለምክር ቤቱ አቅርቧል፡፡

ምክር ቤቱም በሪፖርቱና ውሳኔ ሀሳቡ ላይ በዝርዝር ከተወያየ በኋላ አዋጁ አዋጅ ቁጥር 1159/2011 ሆኖ በሙሉ ድምጽ ፀድቋል፡፡