null The House passed Refugee Law with majority vote.

ምክር ቤቱ ተያያዥነት ያላቸውን ሁለት ረቂቅ አዋጆችን በአብላጫ ድምጽ አፅድቋል፡፡

የኢፌዴሪ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ጥር 9 ቀን 2011 ዓ.ም ባካሄደው 19ኛ መደበኛ ስብሰባው የስደተኞች ጉዳይ ረቂቅ አዋጅን እና በኢትዮጵያ መንግስትና በአለም አቀፍ የልማት ማህበር መካከል ለኢትዮጵያ ኢኮኖሚክ ኦፖርቹኒቲ ፕሮግራም ማስፈጸሚያ የተደረገውን የብድር ስምምነት ለማጽደቅ በተለያዩ ቋሚ ኮሚቴዎች የቀረቡ ሪፖርቶችንና የውሳኔ ሃሳቦችን መርምሮ በአብላጫ ድምጽ አጽድቋል፡፡

የህግ፣ ፍትህና ዲሞክራሲ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ እና የውጭ ግንኙነትና የሰላም ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴዎች የስደተኞች ጉዳይ ረቂቀ አዋጅን በተመለከተ ያቀረቡትን ሪፖርትና የውሳኔ ሃሳብን በሚመለከት ምክር ቤቱ ተወያይቷል፤ ስደተኞችን ስንቀበል ከጥቅሙ ጉዳቱ እንዳያመዝን አቅምን ግምት ውስጥ ማስገባት አለበት፤ በአዋጁ ዙሪያ ክልሎችን ለምን አላወያያችሁም? የእርሻና መስኖ መሬትን በሊዝ የመስጠቱ ጉዳይስ እንዴት ይታያል? የሚሉ ጥያቄዎችና አስተያየቶች ተነስተዋል፡፡

የህግ፣ ፍትህና ዲሞክራሲ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ የተከበሩ ወ/ሮ ፎዚያ አሚን የተቸገሩ ስደተኞችን ተቀብሎ ማስተናገድ የአገራችንን ስም ከፍ ከማድረግ አንጻር የራሱ አስተዋጽኦ እንዳለውና በዚህ ምክንያት የምናገኘው ብድርና ገንዘብ አገራችንን ሃምሳ በመቶ ተጠቃሚ እንደሚያደርጋትና ህግ ሳይወጣለትም እስካሁን አገራችን በተግባር እየሰራችው እንደሆነ ገልጸው ስደተኞቹ የሚቆዩት ችግሩ እስኪቀረፍና አገራቸው እኪረጋጋ ድረስ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡

ክልሎችን ከማወያየት አንጻር ምክር ቤቱ የሁሉም ክልሎች ተወካዮች ያሉበት እንደመሆኑ የክልሎችን ፍላጎት በዚሁ ተፈትሿል የሚል እምነት እንዳላቸውና በተጨማሪም ሁለት ጊዜ የህዝብ ይፋ ውይይት በሚዲያ ጠርተው ያወያዩ መሆኑን አብራርተዋል፡፡

የመሬትና መስኖ እርሻ አጠቃቀምን በሚመለከትም በየሰባት አመቱ ቼክ የሚደረግና የሚታደስ እንደሆነ ገልጸዋል፡፡

አዋጁም አዋጅ ቁጥር 1110/2011 ሆኖ በሶስት ተቃውሞ እና በአንድ ድምጸ ተአቅቦ በአብላጫ ድምጽ ጸድቋል፡፡

የገቢዎች፣ በጀትና ፋይናንስ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ በኢትዮጵያ መንግስት እና በአለም አቀፍ የልማት ማህበር መካከል ለኢትዮጵያ ኢኮኖሚክ ኦፖርቹኒቲ ፕሮግራም ማስፈጸሚያ የተደረገውን የብድር ስምምነት ለማጽደቅ የቀረበ ረቂቀ አዋጅን በሚመለከት ያቀረበው ሪፖርትና የውሳኔ ሃሳብ ላይ ምክር ቤቱ ተወያይቷል በውይቱ በዜጎች ላይ ዕዳ መጨመር አስፈላጊ አይደለም፤ ብድር ተቀብለን ስደተኞችን ማስተናገድ ተገቢ ነው ወይ? የሚሉ አስተያየትና ጥያቄዎች ተነስተዋል፡፡

የቋሚ ኮሚቴው ሰብሳቢ ወ/ሮ ለምለም ሃድጎ ሲመልሱ አገራችን ብድር ሳትቀበልም ስደተኛችን እያስተናገደች እንደሆነና ብድሩ ከወለድ ነጻ በመሆኑ ሰባ በመቶ ለአገራችን የሚውል ሲሆን ሰላሳ በመቶ የሚሆነው ደግሞ ለስደተኞች በመሆኑ በአብዛኛው አገራችን ተጠቃሚ እንደምትሆን ገልጸዋል፡፡

አዋጁም አዋጅ ቁጥር 1111/2011 ሆኖ በሶስት ተቃውሞ እና በሶስት ድምጸ ተአቅቦ በአብላጫ ድምጽ ጸድቋል፡፡

በመጨረሻም ምክር ቤቱ የምክር ቤቱን 4ኛ አመት የስራ ዘመን 18ኛ መደበኛ ስብሰባ ቃለ ጉባኤ መርምሮ በሙሉ ድምጽ አጽድቋል፡፡