null The House urged Ministry of trade to work on modernizing the sector and protecting the illegal trade expansion.

የንግድ ስርዓቱ አለመዘመንና ህገ-ወጥነት መበራከት የንግድ ስርዓቱን እንዳዛባ   በጥንቃቄ መሰራት እንዳለበት ተገለፀ፡፡

የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በ21ኛው መደበኛ ስብሰባው የንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር የ2011 በጀት ዓመት የ6 ወራት የእቅድ አፈጻጸም ሪፖርትን አዳምጧል፡፡

በወቅቱም ከምክር ቤት አባላት፣ ከቋሚ ኮሚቴውና ከህብረተሰቡ ለተነሱ ጥያቄዎች የሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ አመራሮች ምላሽ ሰጥተዋል፡፡

የንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ሚኒስትር ወ/ሮ ፈትለወርቅ ገ/እግዚአብሔር መ/ቤቱ በበጀት ዓመቱ ሰፊ የኢኮኖሚ እድገት ቀጣይነትን ለማረጋገጥ የዘርፉን አቅም የበለጠ ለማሳደግ ሃገሪቱ በምትከተለው የነጻ ገበያ ኢኮኖሚ ፖሊሲ መሰረት የንግድ ስርዓት ግልጽ፣ ተደራሽና ውድድር ላይ የተመሰረት የሸማቹን ማህበረሰብ ጤንነትና ደህንነት በዘላቂነት ማረጋገጥና ላወጣው ዋጋ ተመጣጣኝ የሆኑ ምርቶችንና አገልግሎቶችን እንዲያገኝ ሁኔታዎችን ማመቻቸት እንደሚገባ ገልፀዋል፡፡

ከዚህም ጎን ለጎን የንግዱን ማህበረሰብ ከጸረ ውድድር ተግባር ለመታደግ፣ የሀገር ውስጥ ባለ ሃብቶች በማምረት ተጠቃሚነታቸውም እንዲረጋገጥ ድጋፍ መስጠትና ሀገሪቱ በዓለም የንግድ ስርዓት ተሳታፊና ተጠቃሚ ለማድረግ ዋና ዋና አላማ አድርጎ እየተሰራ እንደሆነ ነው የገለጹት፡፡

መ/ቤቱም የንግድ ስርዓት ዘመናዊ፣ ፍትሃዊና በውድድር ላይ የተመሰረተ በማድረግ ምርትና ምርታማነትን በማሳደግ ብሎም ቀልጣፋና የላቀ የገበያ ማስፋፊያና ትስስር ስርዓት በመገንባት የውጭ ምንዛሬ ለማግኘት የትኩረት መስኮች መለየታቸውንም ጨምረው ገልጸዋል፡፡

ምክር ቤቱ በበኩሉ የንግድ ምዝገባና ፍቃድ አገልግሎት አሰራር ሥርዓትን ከማዘመን ጋር ተያይዞ በጣቢያዎች ደረጃ የሚሰጠው አገልግሎት በኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ለማስደገፍ የተጀመረው ፕሮጀክት ተጠናቆ ሙከራ ላይ መሆኑ የሚደገፍ ቢሆንም ህጋዊ መስመሩን ተከትሎ የሚሰሩ የንግዱ ማህበረሰብ ቁጥር ዝቅተኛ በመሆኑ በቀጣይ የሚኒስቴር መ/ቤቱን የቁጥጥርና ክትትል ስራ ይበልጥ እንደሚጠይቅ ጠቁሟል፡፡

ቀልጣፋና የላቀ የገበያ ማስፋፊያ ትስሰር ስርዓት በመገንባት የተሻለ መዳረሻዎችን ለመፍጠር እስከ 2020 ድረስ አገሪቱ የአለም ንግድ ድርጅት አባል ለማድረግ የሚያስችል ስራዎች እየተሰሩ እንደሆነ ቢብራራም የወጪ ንግድ ከጊዜ ወደ ጊዜ ዝቅተኛ እየሆነ መምጣቱ አሳሳቢ እና ለአብነትም በወርቅ ገበያ ላይ እየታየ ያለው ህገ ወጥነት አንዱ መሆኑን፣ በቡናና ሰሊጥ ላይም በተመሳሳይ ዘመናዊ የምርት ሂደት አለመኖር አገሪቱ በምታመርተው ልክ የውጭ ምንዛሬ ተጠቃሚ እንዳትሆን ከማድረጉም ባሻገር እየታየ ያለው የንግድ ስርዓታችን ለታቀደው የዓለም ንግድ አባልነት የሚመጥን እንዳልሆነ ተነስቷል፡፡

በተመሳሳይ በግርና ምርቶች ላይም የዋጋ አለመመጣጠን፣ በሚፈለገው መጠንና ጥራት አለመመረት፣ የገበያ ዋጋ መውረድ፣ የግብይት ስርዓት መጓተት እና በምርቶች ላይ እሴትን ጨምሮ ወደውጪ አለመላክ በምክንያትነት ተነስተዋል፡፡

በመጨረሻም ም/ቤቱ በከፍተኛ የመንግስት ድጎማ እየቀረበ ባለው ነዳጅና በመሰረታዊ ሸቀጦች መመሪያ መሰረት ለሁሉም ክልሎችና ከተማ አስተዳደሮች ምርቶች ፍትሀዊ ድልድል እና ተደራሽነትን ለማረጋገጥ እየተሰራ ቢገኝም በክትትል ሥራ መላላትና የስርጭት ችግር የተነሳ ማህበረሰቡን ፍላጎት ለማርካት እንዳልተቻለ እና ባጠቃላይ ህገ- ወጥነት መበራከት የንግድ ስርዓቱን በማዛባት ሊጨበጥ ወደማይችል ደረጃ እንዳያደርሰው ሚኒስቴር መ/ቤቱ በጥንቃቄ መስራት እንዳለበት አሳስቧል፡፡