null The Human Resource Development and Technology affair standing committee evaluated the Science and Higher Education Minister of the 100 days performance.

የሰው ሃበት ልማትና ቴክኖሎጂ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር የ2011 ዕቅድና የ100 ቀን ዕቅድ አፈጻጸም ላይ ተወያይቷል፡፡

በውይይቱ ፍትሃዊ ያልሆነ የከፍተኛ ትምህርት ተሳትፎ፣ ዝቅተኛ የግሉ ዘርፍ ተሳትፎ የሚስተዋልበት ከፍተኛ ትምህርት ስርዓትኢንዱስትሪ በሚፈልጋቸው መስኮች በእውቀት፣ ክህሎትና አመለካከት በበቂ ያልተዘጋጀ ምሩቅ ከየተቋማቱ መውጣቱ፣ ተገቢነቱና ጥራቱ ከፍተኛ ክፍተት የሚታይበት የምርምርና ቴክኖሎጂ ሸግግር ስራከኢንዱስትሪውና ከአካባቢ ማህበረሰብ ጋር በተገቢው መጠን ያልተቆራኘ የከፍተኛ ትምህርት እና ቴክኒክና ሙያ ትምህርትና ስልጠና የሚሉትና ሌሎች ችግሮችን መቅረፍ የእቅዳቸው መነሻዎች መሆናቸውን የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር ሚኒስትር ዶ/ር ሂሩት ወልደማሪያም  ጠቁመዋል፡፡

በመቶ ቀናት ውስጥ ከተከናወኑት ተግባራት ሚኒስቴሩን የማደራጀት፣ የዩኒቨርሲቲ ቦርድ አመራሮችና ፕሬዝዳንቶች ጾታን፣ ብሄርን፣ በዋናነት ሜሪትን መሰረት ያደረገ ምደባ መከናወን፣ ለተማሪዎች የተለያዩ የማነቃቂያ ስልጠናዎች መሰጠታቸውን፣ ሰላማዊ የመማር ማስተማር ዙሪያ የተለያዩ ውይይቶች  እየተደረጉ መሆኑን አንስተዋል፡፡

የትምህርት ጥራትን ለማስጠበቅ አንድ ቡድን ተደራጅቶ ጥናት በማካሄድ ላይ መሆኑን፣ የሳይንስ ላቦራቶሪዎችና የኢንጂነርንግ ዎርክሾፖችን ደረጃ ለመወሰን የተዘጋጀውን ስታንዳርድ ማጠናቀቅና ወደ ሥራ እንዲገባ ለዩኒቨርሲቲዎች መላኩን ጠቁመው፤ የከፍተኛ ትምህርት ጾታዊ ምጥጥን ዙሪያም እየሰሩ እንደሆነ፣ የቴክኒክና ሙያ ትምህርት ለማጠናከር የሚረዱ የተለያዩ የውይይት መድረኮች መኖራቸውን ገልጸዋል፡፡

ሃሰተኛ የትምህርት ማስረጃ መለየት የሚያስችል መሳሪያ ተዘጋጅቶ በስራ ላይ ሊውል እንደሆነና የጥናታዊ ጽሁፍ ኩረጃን ማስቀረት የሚያስችል ቴክኖሎጂም እንደተዘጋጀ አብራርተዋል፡፡

የቋሚ ኮሚቴው ሰብሳቢ የተከበሩ ወ/ሮ እምየ ቢተው አጠቃላይ የተሰጡ ማብራሪያዎች ጥሩ መሆናቸውን ገልጸው የ2011 ዕቅድ ዝርዝር ተግባራትን የያዘ ቢሆንም የተሟላ ዕቅድ እንዳልሆነና በቢኤስሲ መሰረት በአራቱ ዕይታዎች መታቀድ እንዳለበት እና እቅዱ በሚገባ ተከልሶ በአጭር ጊዜ ሊደርሳቸው እንደሚገባ ጠቁመዋል፡፡

የመቶ ቀናት ዕቅድ አፈጻጸም በሚመለከት የተጀመሩ ስራዎች ጥሩ ቢሆኑም አብዛኞቹ ሂደት ላይ ያሉ በመሆናቸው ባለው ጊዜ  መጠናቀቅ እንዳለባቸው ገልጸዋል፡፡

ሰላማዊ የመማር ማስተማር ለመፍጠር ልዩ ዕቅድ ማቀድና በንቃት መከታተል እንደሚያስፈልግና በአጭር ጊዜ ሊፈቱ የሚገባቸው ጉዳዮች ተለይተው መቀመጥ እንዳለባቸውም አንስተዋል፡፡

የስራ መደብ የሌላቸው የትምህርት መስኮችን በሚመለከት ጥናት ማድረግ፣ የክትትልና የቁጥጥር ስርአት ማጠናከር፣ ከባለድርሻ አካላት ጋር የመናበብ እና ገበያው የሚፈልገውን የሰው ሃይል ማፍራት እንደሚያስፈልግ እንዲሁም ዩኒቨርሲቲዎችን ከኢንዱስትሪው ጋር የማስተሳሰር ስራ መስራት እንደሚያስፈልግ ኮሚቴው አንስቷል፡፡ ሙስናና ኪራይ ሰብሳቢነትን የማስወገድ የውስጥ ኦዲተር የማጠናከር ተግባራት ትኩረት ሊሰጣቸው እንደሚገባ ገልጿል፡፡

ከቋሚ ኮሚቴው የተነሱ አስተያየቶችና ጥያቄዎች ተገቢ መሆናቸውንና በቀጣይ መስተካከል ያለባቸው ጉዳዮች ተስተካክለው እንደሚያቀርቡ የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር ሚኒስትር ዶ/ር ሂሩት ወልደማሪያም እና ሌሎች የስራ ሃላፊዎች ገልጸዋል፡፡