null The Ministry of Defense a bled to control the conflicts challenging the state existence.

መከላከያ ሚኒስቴር የአገር ህልውና የሚፈታትኑ ግጭቶችን ለመቆጣጠር መቻሉን አስታወቀ፡፡

በሱማሌ፣ በኦሮሚያና በቤኒሻንጉል ጉሙዝ፣ በቅማን እና በሌሎች አካባቢዎች የነበሩ ግጭቶች አገር ማፍረስ ደረጃ ላይ የሚወስዱ ቢሆኑም መከላከያ ሰራዊት ባደረገው ዕልህ አስጨራሽ ጥረት ሰላም ለማረጋገጥና መረጋጋት ለመፍጠር መቻሉን ጀነራል ብርሃኑ ጁላ የጦር ሃይሎች ምክትል ኤታማዦር ሹም አስታወቁ፡፡

መከላከያ ሰራዊቱ ህገ መንግስቱን መሰረት አድርጎ የአገሪቷን ሰላም እየጠበቀ ባለበት ወቅት ደረጃውን የሚያሳንስና የመበታተን አደጋ እንዲገጥመው የተወሰኑ ሃይሎች እየሰሩበት በመሆኑ ይህን ስጋት ምክር ቤቱም ጉዳዬ ነው ብሎ እንዲከታተልም አሳስበዋል፡፡ በወለጋ ዞኖች የነበረውንም የፀጥታ ስጋት ለመፍታት በተሰራው ስራ ወደ ዞኖቹ ከተሞችና ዋና ዋና ወረዳዎች የሚወስዱ መንገዶች መከፈታቸውን ጠቁመው ህዝቡም በነበረው ሁኔታ በመደናገጥ ሰራዊቱ እንዲገባለት ጥሪ ማቅረቡንም ለምክር ቤቱ ጠቁመዋል፡፡

መከላከያ ሚኒስቴር ያቀረበውን 6 ወራት ዕቅድ አፈፃፀምን አስመልክቶ በቋሚ ኮሚቴውም ሆነ በምክር ቤቱ አባላት ለቀረቡት ጥያቄዎች ጀነራል ብርሃኑ ጁላ እና የኢፌድሪ የመከላከያ ሚኒስትር ኢንጅነሪ አይሻ መሃመድ ምላሽ ሰጥተዋል፡፡

 ኢንጅነሪ አይሻ መሃመድ ሙስናን አስመልክቶ ለቀረቡላቸው ጥያቄዎች በሰጡት ማብራሪያ የሙስና  መከላከያ ስትራቴጂ ተዘጋጅቶ ለሙስና ተጋላጭ ናቸው ባልናቸው የስራ ክፍሎች ጋር ውይይት አድርገናል ብለዋል፡፡በሌላ መልኩ ሁሉም የጸጥታ አካል የራሱ የስራ ድርሻ ያለው ቢሆንም የክልል የጸጥታ አካላት ላይ የአቅም ግንባታ ስራ ሊሰራ እንደሚገባም ጠቁመዋል፡፡

ሚኒስትሯ በወሰን ይገባኛል እና በማንነት ምክንያት የሚፈጠሩ የጎሳ ግጭቶች እና የውጭ ምንዛሪ እጥረት ምክንያት ለበርካታ የስራ መጓተቶች ምክንያት በመሆኑ በዚህ ዙሪያ ምክር ቤቱ ሊያግዘን ይገባል ብለዋል፡፡

የውጭ ግንኙነት እና የሰላም  ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ አቶ ተስፋዬ ዳባ በበኩላቸው በሃገራችን የተጀመረውን የለውጥ ሂደት ለመቀልበስ የተነሱትን ጸረ ሰላም ኃይሎች ለመታገል የመከላከያ ሰራዊታችን የሰላም ማስከበር ስራ ላይ ውጤታማ በመሆን የኢትዮጵ ህዝቦች አለኝታነቱን  በማሳየት እና ህገ መንግስታዊ ስርአቱን ከአደጋ ለመጠበቅ የተሰራውን ስራ ቋሚ ኮሚቴው በጥንካሬ ተመልክቶታል ብለዋል፡፡