null The Ministry of Water, irrigation and Energy of the first quarter performance is low.

የውሃ፣መስኖና ኢነርጂ ሚኒስቴር የ1ኛ ሩብ ዓመት አፈጻጸሙ ዝቅተኛ እንደሆነ ተገለጸ፡፡

ታህሳስ 19 ቀን 2011ዓ/ም በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የተፈጥሮ ሀብት፣መስኖና ኢነርጂ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ የውሀ፣መስኖና ኢነርጂ ሚኒስቴርን የ2011 በጀት ዓመት የ1ኛ ሩብ ዓመት የእቅድ አፈጻጸም ሪፖርት በገመገመበት ወቅት ነው የብዙ ፕሮጀክቶች አፈጻጸም ዝቅተኛ እንደሆነ የተገለጸው፡፡

የረጲ ደረቅ ቆሻሻ የሀይል ማመንጫ ጣቢያን ጨምሮ ግንባታቸው ተጠናቆ ሀይል ማመንጨት የጀመሩ ፕሮጀክቶች አሁን ላይ የተወሰኑት ማቆማቸውን የገለጹት የቋሚ ኮሚቴው አባላት መሰረታዊ ችግሮቻቸው ተለይተው መፈታት እንዳለባቸው ተናግረዋል፡፡

በተመሳሳይም በተለያዩ ክልሎች ተጀምረው ለዘመናት ባልተጠናቀቁ ፕሮጀክቶች ላይ ህዝቡ ከፍትኛ ቅሬታ ስለሚያነሳ ለመልካም አስተዳደር ችግሮች መፈጠር መንስኤ  መሆናቸው የሚያመላክቱ  ነገሮች እንዳሉ ተጠቁሟል፡፡

የውሀ፣መስኖና ኢነርጂ ሚኒስቴር ሚኒስትር ደክተር ስለሺ በቀለ ከታላቁ የህዳሴ ግድብ ጋር በተያያዘ የፕሮጀክቱ ግንባታ መጓተት፣የሀብት ብክነት፣የግንባታ ጥራቱን እና ሌሎች ተያያዥ ችግሮችን አስመልክቶ በህዝቡ ዘንድ የተፈጠረውን አሉታዊ ስሜት ቀድሞ ወደ ነበረበት ለመመለስ ከወዲሁ ምን እየተሰራ ነው ሲሉ ከቋሚ ኮሚቴው አባላት ለተነሱላቸው  ጥያቄዎች ምለሽ በሰጡበት ወቅት ግድቡ መሰረታዊ ችግሮች እንዳሉበት ተገምግሞ የማስተካከያ ስራ እየተሰራ እንደሆነ አስረድተዋል፡፡

የህዝቡንም ስሜት ቀድሞ ወደነበረው ስሜት ለመመለስ በቅርቡ የፓናል ውይይት ተካሂዶ እንደነበር እና መጠይቆችም ተበትነው በተገኘው የዳሰሳ ውጤት ህዝቡ ተስፋ እንዳለው ያመላክታል የሚል ከሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ አመራሮች የቀረበ ቢሆንም የቋሚ ኮሚቴው አባላት በበኩላቸው ህዝቡ አሁንም ጥርጣሬ ውስጥ ነው፣ የጥናቱ ውጤት የተሳሳተ ነው፣እንደገና በሰፊው መታየት ሲሉ ተቃውሟቸውን አሰምተዋል፡፡

በንፁህ ውሀ መጠጥ አቅርቦት ላይ የሚገጥመውን ተግዳሮት ስር ነቀል በሆነ መንገድ ለመፍታት  ዘርፈብዙ ስራዎች እየተከናወኑ እንደሆነ የገለጹት ሚኒስትሩ ዶክተር ስለሽ ድርቅ በሚበረታባቸው እና በበረሀማ አካባቢዎች ጥልቅ የውሀ ጉድጓዶች ተቆፍረው ዜጎች ንጹህ ውሀ የሚገኙበትን መንገድ ለማመቻቸት በዘርፉ በለሙያዎች ጥናት እየተደረገ መሆኑን አስገንዝበዋል፡

የቋሚ ኮሚቴው አባላት በበኩላቸው በአገሪቱ አንዳንድ አአካባቢዎች  የሚቆፈሩ ጥልቅ የውሀ ጉድጓዶች ለማህበረሰቡ ተገቢውን አአገልግሎት እየሰጡ እንዳልሆነ ገልጸው ችግሮች በደንብ ሊታዩና ሊፈተሹ  እንደሚገባ ነው የጠቆሙት፡፡

የቋሚ ኮሚቴው ሰብሳቢ የተከበሩ ወ/ሮ ፈቲያ የሱፍ በበኩላቸው ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ በ1ኛ ሩብ ዓመት ካከናወናቸው ተግባራት የስራ እደድል ፈጠራን፣ የንጹህ ውሀ መጠጥ አቅርቦት ፕሮጀክት ፕሮግራም፣የከርሰ ምድር ውሀ የድዛይን ጥናቱን በጥንካሬነት አንስተው፣በመስኖ ተፋሰስ ስራዎች፣በኢነርጂና በውሃ ሀብት አስተዳደር አንጻር እጥረቶች እንዳሉ አስረድተዋል፡፡

በተመሳሳይም በኤሌትሪክ ሀይል ዙሪያ ከሀይል ማከፋፈያና ማስተላለፊያ ዝረጋታ ሰፊ ስራ መሰራቱን በጥንካሬነት የገለጹ ሲሆን ታላቁን የህዳሴ ግድብ ጨምሮ በመግነባት ላይ ያሉ ፕሮጀክቶች መሰረታዊ ክፍቶች እንዳሉባቸው አስረድተዋል፡፡ የአይሻ ቁትር 2 የነፋስ ሀይል ማመንጫ ጣቢያም አፈጻጸሙ ዝቅተኛ እነደሆነ አያይዘው ጠቁመዋል፡፡

በመጨረሻም የ2011 በጀት ዓመት የውጤት መመዘኛ መስፈርቶች እና በእቅድ ቁልፍ ተግባራት ክብደት አሰጣጥ ዙሪያ ሰፋ ያለ ውይይት ተደርጓል፡፡