null The Ombudsman should be focusing on the provisions of proclamation.

የህዝብ እምባ ጠባቂ ተቋም ማቋቋሚያ አዋጅ ማሻሻያ ተቋሙን አላሰራም ባሉ ድንጋጌዎች ላይ ማተኮር እንደሚገባ በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የህግ፣ ፍትህና ዲሞክራሲ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ አሳሰበ፡፡

የህዝብ ዕምባ ጠባቂ ተቋም ማቋቋሚያ አዋጅ አገሪቱ ካለችበት የዕድገት ደረጃ፣ ካለው አገራዊ ለውጥና ከዓለም አቀፍ ሁኔታ ጋር እንዲጣጣም የሚያስችል ሁኔታ ተሻሽሎ ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ቀርቦ ምክር ቤቱ ለዝርዝር ምርመራ ለህግ፣ ፍትህና ዴሞክራሲ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ መመራቱ ይታወቃል፡፡ በዚህ መሰረት ቋሚ ኮሚቴው ከተቋሙ የስራ ሃላፊዎችና ባለሙያዎች ጋር ታህሳስ 15 ቀን 2011 ዓ.ም በረቂቅ አዋጁ ላይ ውይይት አድርጓል፡፡

በውይይቱ ከተነሱ ጉዳዮች አንዱ ተቋሙ አሳሪ የሆነ ውሳኔ ያስተላልፍ ወይስ ውሳኔ ለሚሰጡ የመንግስት አካላት ምክረ - ሃሳብ ያቅርብ የሚለው ነው፡፡ የቋሚ ኮሚቴው አባላት ወደአንድ ሃሳብ ያለመምጣታቸውን ከሰጡት አስተያየቶች ለመረዳት የተቻለ ሲሆን ተቋሙ ግን ከዓለም አቀፍ ልምድ አንፃር ስልጣኑ ምክረ ሃሳብ ማቅረብ ላይ ብቻ እንዲሆን ፍላጎቱ መሆኑን በመጠቆም የምርመራ፣ የቁጥጥርና የጥናት ውጤቶችን አስመልክቶ በመገናኛ ብዙሃን ይፋዊ መግለጫ የሚሰጥበትንና በስም ማጥፋት የማይጠየቅበትን ሁኔታ ከተመቻቸለት ሃላፊነቱን ሊወጣ እንደሚችል ነው ያመለከተው፡

ሌላው የውይይት ነጥብ ለተቋሙ የሚቀርቡ አቤቱታዎች በአጭር ጊዜ ውስጥ ምላሽ ያገኛሉ እና አቤቱታ አቅራቢው ላይ የማይመለስ ወይም የማይተካ ጉዳት የሚያደርሱ ጉዳዮች ምርመራቸው እስከሚጠናቀቅ ድረስ ታግደው ይቆያሉ የሚሉ ድንጋጌዎች ናቸው፡፡ እነዚህ ድንጋጌዎች የጊዜ ጣሪያ ሊቀመጥላቸው እንደሚገባ አባላት አስተያየቶቻቸውን አቅርበዋል፡፡ የጊዜ ገደቦቹ ለዜጎች መብትንና ለተቋሙ ግዴታዎችን ስለሚያቋቁሙ በደንብ እንዲፈተሹ አባላቱ አሳስበዋል፡፡ ተቋሙ በበኩሉ የጊዜ ጣሪያ ከማመልከት ይልቅ እንደጉዳዩ ክብደት ደረጃ እየታየ እልባት ቢሰጥ የሚል መከራከሪያ ነጥብ አንስተዋል፡፡

ከነዚህ ባሻገር የፀጥታ አካላት የሚያደርሱትን በደል ተቋሙ የሚያይበት ድንጋጌ በረቂቁ ቢካተት፣ የተቋሙ ሂሳብ ምክር ቤቱ በሚሰይመው አካል ሳይሆን በዋና ኦዲተር ቢመረመር፣ የዕምባ ጠባቂ ጉባኤ የቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት ሃላፊዎችን መልምሎ ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ለሹመት የሚያቀርብበት አሰራር ቢዘረጋ፣ የህዝብ ዋና እምባ ጠባቂ የስራ ጊዜ ከ6 – 7 ዓመት ሆኖ እንደገና የመመረጥ ጉዳይ ቢቀር የሚሉ እና ሌሎች መሰል አስተያየቶችን ከአባላቱ ቀርበው የተቋማቱ ሃላፊዎችና ባለሙያዎች ምላሽ ሰጥተዋል፡፡

የቋሚ ኮሚቴው ሰብሳቢ የተከበሩ ወ/ሮ ፎዚያ አሚን የቅርንጫፍ ጽህፈት ቤቶች ሃላፊዎች አሿሿም፣ ስለዕግድ ጊዜ፣ የዋና እምባ ጠባቂ የአገልግሎት ዘመን እና ሌሎች ጉዳዮች ላይ ያላቸውን አስተያየት አቅርበው ረቂቅ ህጉ የበለጠ እንዲዳብር የህዝብ አስተያየት መስጫ መድረክ እንደሚዘጋጅ አሳስበዋል፡፡