null The security of finance and information center should focus on preventing money laundering and supporting terrorist.

የፋይናንስ ደህንነት መረጃ ማዕከል በህገ-ወጥ የገንዘብ ዝውውርና ሽብርተኝነትን በገንዘብ ለመደገፍ የሚደረጉ ሙከራዎችን በመከላከል ላይ ጠንከሮ መስራት እንዳለበት ተገለፀ፡፡

ይህ የተጠቆመው የውጭ ግንኙነትና የሰላም ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ በማዕከሉ የመስክ ምልከታ ባደረገበት ወቅት ነው፡፡

በምልከታውም የማዕከሉ ዋና ዳይሬክተር አቶ ኪዳነማሪያም ገ/ፃዲቅ ማዕከሉ የተቋቋመው በህገ-ወጥ መንገድ የተገኘ ገንዘብን ህጋዊ አስመስሎ በማቅረብ እና ሽብርተኝነትን በገንዘብ መርዳትን ለመከላከል በወጣው አዋጅ ቁጥር 780/2005 መረሰት ኢትዮጵያ የአለም አቀፍ ስምምነት በመፈረሟ እንደሆነና ማዕከሉ በዋናነት የሚሰራቸው ስራዎችም መረጃን የማሰባሰብ፣ የመቀበል፣ የማከማቸት፣ የመመርመር፣ የመተንተን፣ የማሰራጨት፣ የህብረተሰቡ ግንዛቤ እንዲዳብር እና ቁጥጥር፣ ክትትልና ፍተሻ የማድረግ ስራ እንደሆነ ገልጸዋል፡፡

ማዕከሉም በበጀት ዓመቱ በርካታ የህገ ወጥ ስራዎችን ለመከላከል ባደረገው እንቅስቃሴ መሰረት 309 የሚሆኑ ተጠርጣሪ ግብይቶችን ውስጥ 21 ወንጀል ነክ፣ 7 በሪል ስቴትስ፣ 9 ህንጻ ባለሙያዎች፣ 7 በሂሳብ ባለሙያዎችና 14 ፌዴራል ፖሊስ ላይ የተለያዩ አስፈላጊ መረጃዎችን መሰብሰብና ማደራጀት ተችሏል ብሏል፡፡

ቋሚ ኮሚቴው በአገር ውስጥ አሁን አሁን ግለሰቦች ከሚያገኙት በላይ ሃብት እያከማቹ በተለይ ሽብርተኝነትን በገንዘብ የመደገፍ ሙከራዎች እና ህገ ወጥ የገንዘብ ዝውውር በስፋት እየተደረገ በመሆኑ መረጃውን በተደራጀ መንገድ በመሰብሰብ ቀድሞ ለመከላከል በማዕከሉ እየተሰራ ያለው ስራ በቂ እንዳልሆነና ለዚህም የተደራጁ መረጃዎች በሚመለከተው አካል ወደ እርምጃ የመቀየሩ ሂደት በጣም ዝቅተኛ መሆኑ እንደማሳያ ተነስቷል፡፡

ማዕከሉ ከዚህ በፊት በሰራው ስራ ከ300 ሺህ በላይ ህገ ወጥ የጥሬና የሃዋላ ገንዘብ ዝውውርን ለመቆጣጠር ቢሰራም የወንጀል ፍሬ ያለማስመለሱ መሰረታዊ ችግር ሆኖ በአለም ካሉት የወንጀል መጠቀሚያ አገራት ከሚባሉት ኢራንና ሰሜን ኮሪያ አንድ ደረጃ ከፍ ብላ እንድትቀመጥ እንዳደረጋት ለቋሚ ኮሚቴው ተብራርቷል፡፡

ቋሚ ኮሚቴው በበኩሉ አገሪቱ የውጭ ቀጥተኛ ኢንቨስትመንት ለመሳብ በርካታ ወጪ በማውጣት መሰረተ ልማት እያስፋፋች ባለችበት ሁኔታ ላይ የፋይናንስ ስርዓቱ በዚህ መልኩ መውረዱ ጉዳቱ ከፍተኛ እንዳያደርገው በጥንቃቄ መሰራት እንዳለበት ጠቁሟል፡፡

የማዕከሉ መጠናከር የአገር ሰላምና ደህንነትን በማረጋገጥ ብሎም ህገ-ወጥነትን በመከላከል አገሪቱ ማግኘት የሚገባትን የውጭ ምንዛሬ እንድታገኝ ጉልህ ድርሻ ያለው ቢሆንም እስካሁን ተገቢውን ትኩረት ካለመሰጠቱም አልፎ በተለያዩ አካላት ተፅዕኖ ስር በመሆኑ የሚፈለገውን ያክል እንዳይሰራና አፈጻጸሙንም ዝቅተኛ እንዳደረገውም ቋሚ ኮሚቴው አንስቷል፡፡

በመጨረሻም ቋሚ ኮሚቴው በበጀት ዓመቱ ማዕከሉ ካለበት ከፍተኛ የሰው ሃይል፣ የተደራጀ የመረጃ ደህንነት ለማስጠበቅ የተሽከርካሪ እጥረትና የመረጃ ትንተና ሶፍትዌር ክፍተቶችን ለመቅረፍ እየሰራ ቢሆንም በቀጣይም ችግሩ ተባብሶ አገሪቱ ወደ ተሻለ ደረጃ እንዳትደርስ እንቅፋት የሆኑ ችግሮቹን በመቅረፉ ረገድ የሁሉም ህብረተሰብ ድጋፍ እንደሚያስፈለግ በምልከታው ወቅት አሳስቧል፡፡