null The Sekota-Tekeze pure drinking water project is not started yet, unless reports since 2014.

የሰቆጣ ተከዜ ንጹህ መጠት ውሃ ፐሮጀክት ከ2006 ዓ.ም ጀምሮ ከሪፖርት የዘለለ በቦታው የተጀመረ ስራ እንደሌለ ተጠቆመ፡፡

ይህ የተባለው የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የተፈጥሮ ሃብት፣ የውሃ መስኖና ኢነርጂ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ የአስፈጻሚ መስሪያ ቤቶችን ሪፖርት መሰረት በማድረግ ፕሮጀክቱ የደረሰበትን ደረጃ እና ውጤታማነት ለማረጋገጥ ባደረገው የመስክ ምልከታ ነው፡፡

ከተከዜ ግድብ ጋር ተያይዞ በፌደራል መንግስት እና በኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ሃይል በሰቆጣ 3 ወረዳዎች በ16 ቀበሌዎች ይሰራል ተብሎ የታቀደው የንጹህ መጠጥ ውሃ ፕሮጀክት ከሪፖርት ያለፈ የተሰራ ስራ እንደሌለ ቋሚ ኮሚቴው አረጋግጧል፡፡ በመሆኑም የአካባቢው ማህበረሰብ ለከፍተኛ የመጠጥ ውሃ ችግር መጋለጡን ቋሚ ኮሚቴው በምልከታው ማወቅ ችሏል፡፡

ይህ ፕሮጀክት ስራውን ባለመጀመሩ እና ህብረተሰቡ ያለበትን የመጠጥ ውሃ ችግር ባለመቀረፉ 4 እና 5 ሰአት ጉዞ በማድረግ ውሃ ለመቅዳት በሚደርስባቸው እንግልት ሞትን ጨምሮ ለተለያዩ አደጋዎች እየተዳረጉ መሆናቸውን ከህብረተሰቡ በተገኘ መረጃ ማወቅ ተችሏል፡፡ ቋሚ ኮሚቴው በበኩሉ ባደረገው ምልከታ የውሃ ተቋማቱ አለመኖራቸውን የተመለከተ ሲሆን ለተቋማቱ የተመደበን በጀት አስመልክቶ በአካባቢው አመራር የሚታወቅ እንዳልሆነ እና ፕሮጀክቱ ጥናት ከማካሄድ ያለፈ ከበላይ አካላት የተደረገ ድጋፍና ክትትል እንደሌለ ታዝቧል፡፡

ከዚህ ጋር ተያይዞ የሰቆጣ ከተማ የንጹህ መጠጥ ውሃ አገልግሎት ካለው የህዝብ መጠን ጋር የማይመጣጠን እና ህብረተሰቡ ውሃ የሚያገኘው ከ15-20 ቀናት ቆይቶ በመሆኑ አሳሳቢ ችግር ውስጥ መሆናቸውን ቋሚ ኮሚቴው ተመልክቷል፡፡

በመሆኑም የህብረተሰቡን የንጹህ ውሃ መጠጥ ችግር በመቅረፉ ረገድ የፌደራል መንግስትም ሆነ ጉዳዩ የሚመለከተው ሚንስቴር መስሪያ ቤት የጉዳዩን አሳሳቢነት ታሳቢ በማድረግ የሰቆጣና ተከዜ የንጹህ መጠጥ ውሃና ሳንቴሽን ፕሮጀክት ስራቸውን እንዲጀምሩና ለህብረተሰቡ ተደራሽ እንዲሆን በማድረግ ላይ ትኩረት ተሰጥቶ ሊሰራ እንደሚገባ ቋሚ ኮሚቴው አስገንዝቧል፡፡