null The Speaker of the House Mr. Tagesse Chafo called to strengthen the current country change by improving the participation of women.

የተጀመረውን ሃገራዊ ለውጥ በዘላቂነት ለማስቀጠል ሴቶች ከመቼውም ጊዜ በላይ  ተሳትፏቸውን አጠናክረው እንዲቀጥሉ አፈ-ጉባኤ አቶ ታገሰ ጫፎ ጥሪ አቀረቡ፡፡

በሃገራን እየተካሄደ ያለውን ለውጥ ውጤታማና ዘላቂ ለማድረግ እንዲሁም በብሄር፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች መካከል የመከባበርና የሰላም ባህል እንዲዳብር ለማድረግ በተመራጭ ሴቶች ኮከስ የተዘጋጀና ሰላም ላይ ያተኮረ የፓናል ውይይት በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ተካሂዷል፡፡

የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ-ጉባኤ የተከበሩ አቶ ታገሰ ጫፎ በሃገራችን እዚህም እዛም የሚታዩ ግጭቶችን በዘላቂነት ለመፍታት እና ሰላምን ለማስፈን ሴቶች ንቁና ብቁ ሆነው ተሳትፏቸውን ማጠናከር እንደለባቸው ተናግረዋል፡፡

ግጭቶቹ በለውጥ ሂደት ውስጥ የሚያጋጥሙ ጊዜያዊ ችግሮች መሆናቸውን የገለጹት አቶ ታገሰ፤ በእነዚህ ጊዜያዊ ችግሮችም ቢሆን ክቡር የሆነው የሰው ልጅ ህይወት በምንም ምክንያት ማለፍ የለበትም ሲሉ አሳስበዋል፡፡

ውይይቱን በተመለከተ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የፖለቲካ ሳይንስና አለም አቀፍ ግንኙነት ምሁሩ ፕሮፌሰር ካሳሁን ብርሃኑ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በኢትዮጵያ ሰላም ላይ ሚናው ምን ይመስል እንደነበር ገለጻ አድርገዋል፡፡

በገለጻቸው ምክር ቤቱ አስፈጻሚ አካሉ መጠነ ሰፊ የሰብአዊ መብት ጥሰት ሲፈጸምና በፖለቲካ ተጽዕኖ ውሳኔዎችን ሲወስን ጫናውን ተቋቁሞ ችግሮቹን መፍታትና መቆጣጠር ተስኖት እንደቆየ ተናግረዋል፡፡

አሁን ለተከሰተው የሰላም እጦት ችግር የገዥው ፓርቲ እና የመንግስት አሰራሮች መደበላለቅ፣ የሃገሪቱ ጠቃሚ እሴቶች መሸርሸር፣ ቡድኖችና ግለሰቦች ከህግ በላይ መሆን፣ ችግሮች እስኪከማቹ መጠበቅ፣ የአስፈጻሚ አካሉ ስልጣንን ያለአግባብ የመጠቀም ፍላጎት ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ መሄዱ ዋና ዋና የችግሩ መንስኤዎች መሆናቸውን ፕሮፌሰር ካሳሁን አብራርተዋል፡፡

የህዝብ ውክልና ስራ መስዕዋትነትን ይጠይቃል ያሉት ፕሮፌሰር ካሳሁን፤ ምክር ቤቱ የአስፈጻሚ አካሉን ጫና ተቋቁሞ የውክልና ስራውን በተገቢው ሁኔታ አለመስራቱ በህዝብ ዘንድ ተቀባይነቱንና ተዓማኒነቱን ጥያቄ ውስጥ እንዳስገባውም አክለዋል፡፡

የውክልና ስራችን ህገ-መንግስቱ በሚፈቅደው መሰረት ለመወጣት ስንሞክር በአስፈጻሚ አካሉ በኩል እየተከሰስንና ያልሆነ ስም እየተሰጠን አንደነበርና ይህ አካሄድ ደግሞ በሃገራችን አሁን ለተከሰተው ችግር ዋና መንስኤ እንደነበር አንድ የምክር ቤት አባል አክለዋል፡፡

የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ምክትል አፈ-ጉባኤ የተከበሩ ወ/ሮ ሽታዬ ምናለ በበኩላቸው በቀሪ ጊዜያችን ከህዝብ ጎን በመቆም የህዝብን ጥቅም ባስከበረ መልኩ መንቀሳቀስ ይገባል ሲሉ ገልጸዋል፡፡