null Transport Authority should solve the challenges facing the sectors.

የትራንስፖርት ባለስልጣን በዘርፉ የሚስተዋሉ ብልሹ አሰራሮችን ለማስወገድ እና በትራፊክ አደጋ የሚከሰተውን ሞት ለመቀነስ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በቅንጅት መስራት እንዳለበት ተጠቆመ፡፡

ጥር 22 ቀን 2011 ዓ.ም የኢፌዴሪ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የከተማ ልማት፣ ኮንስትራክሽንና የትራንስፖርት ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ የፌደራል ትራንስፖርት ባለስልጣን የ2011 ዓ.ም የግማሽ አመት ዕቅድ አፈጻጸምን ገምግሟል፡፡

የባለስልጣኑ የፖሊሲ ጥናትና የዕቅድ ዝግጅት ክትትልና ግምገማ ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ፍሰሃ መብራህቶም እንደገለጹት በአሽከርካሪ ብቃት ማረጋገጫ ተቋማት ዙሪያ የሚታዩ ብለሹ አሰራሮችን ለመቀነስ የኪራይ ሰብሳቢነት እና የሀሰተኛ መረጃ ምንጭን ለመከላከል የሚያስችል የመጀመሪያ ረቂቅ ጥናት መዘጋጀቱን፣ በፈቃድ ሰጪ አካላት የሚስተዋሉ ክፍተቶችን በመለየት እንዲፈቱ ለሚመለከተው አካል መተላለፋቸውን አንስተዋል። በዘርፉ የሚስተዋሉ ችግሮችን ለመፍታት ድንገተኛና መደበኛ የቅድመ ስምሪት የቴክኒክ ምርመራዎች ማድረግ፣ አገልግሎቶችን በኢ-ሰርቪስ መደገፍ የመሳሰሉ ተግባራት በመከናወን ላይ መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡

በትራፊክ አደጋ የደረሰው የሞት፣ የከባድና ቀላል ጉዳት ካለፈው አመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር የጨመረ ሲሆን የንብረት ውድመት ግን የመቀነስ ሁኔታ እንደሚታይበት ጠቁመዋል፡፡

ቋሚ ኮሚቴው ባለስልጣኑ በግማሽ ዓመቱ የዕቅድ ዘመን 53 ቋሚ የተሽከርካሪ ቴክኒክ ምርመራ ተቋማት ላይ የተቋማቱ የብቃት ደረጃ ለማረጋገጥ በታቀደው መሰረት መፈጸሙ፣ የ2010 በጀት ዓመትን የፋይናንስ ኦዲት ለማከናወንና የሁለት የስራ ክፍሎችን የክዋኔ ኦዲት ለማድረግ ታቅዶ በግማሽ ዓመቱ በታቀደው መሰረት ማጠናቀቅ መቻሉ፣ የአሽከርካሪ ማሰልጠኛ ተቋማት ላይ ከክልሎች ጋር በመቀናጀት የተደረገው የብቃት ምርመራና ከመስፈርት ውጪ እየሰሩ የተገኙ እርምጃ እንዲወሰድባቸው ለከልሎች መመሪያ መተላለፉን በግብረ መልሱ በጥንካሬ ካነሳቸው ውስጥ ይጠቀሳሉ፡፡

በሌላ በኩል የካፒታል በጀት አጠቃቀም ዝቅተኛ መሆን፣ ፈቃድ ሰጪ የሆኑ አካላትን ብቃት ማረጋገጥና መፈተሽ በታቀደው መሰረት አለመከናወኑ፣ በበጀት ዓመቱ  በተሽከርካሪዎች የትራፊክ አደጋ የሚደርሰውን የሰው ሞት መጠን  ለመቀነስ የታቀደ ቢሆንም በግማሽ ዓመቱ አፈጻጸም የተገኘ ውጤት ካለመኖሩም በላይ ካለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነፃፀር የሞት፣ የከባድና ቀላል ጉዳት መጠን የመጨመር አዝማሚያ በመታየቱ ድጋፍና ክትትሉ ውጤት ያላመጣ መሆኑ፣ግዥዎች በታቀደው የጊዜ ሰሌዳ መሠረት ያለመፈጸማቸውና ታቅደው ያልተከናወኑ ተግባራት መኖራቸውን በእጥረት አንስቶ በቀጣይ ትኩረት ሊሰጣቸው እንደሚገባ  ቋሚ ኮሚቴው አሳስቧል፡፡