null Water is one of the basic needs for human beings and it should be conserved.

ውሃ መሰረታዊ ከሆኑት የተፈጥሮ ሃብቶች አንዱና የህይወት መሰረት በመሆኑ ልዩ ጥበቃና እንክብካቤ ሊደርግለት እንደሚገባ ተገለጸ፣

ይህ የተገለጸው በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የተፈጥሮ ሃብት ልማት፣ መስኖና ኢነርጅ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ በሐዋሳ፣ አብጃታና ሻላ ሀይቆችና ተፋሰሶች ዙሪያ የሚሰሩ የተፈጥሮ ሃብት ስራዎችን በተመለከተበት ወቅት ነው፡፡

በሐዋሳ የስምጥ ሸለቆ ሐይቆች ተፋሰስ ጽ/ቤት የአካባቢ ጥበቃ ከፍተኛ ባለሙያ የሆኑት አቶ አንዱዓለም ገዛኸኝ ለቋሚ ኮሚቴው ባቀረቡት ጥናታዊ ጽሑፍ እንዳሉት በአለማችን ለመጠጥና ለምግብነት የምንጠቀመው የውሃ መጠን 2.4 በመቶውን ብቻ እንደሆነና ከዚህ አኳያ እንደ ውሃ አሳሳቢና ትኩረት የሚፈልግ ሃብት እንደሌለ አስረድተዋል፡፡

በአቅርቦትና ፍላጎት መካከል አለመመጣጠን እንዳለ የገለጹት ባለሙያው ለዚህም ዋና ዋናዎቹ ምክንያቶች የህዝብ ቁጥር መጨመር፣ የአኗኗር ዘይቤ መቀየር፣ የተፈጥሮ ሃብቱ እየወደመ መምጣቱና ያሉትም የውሃ ሃብቶች እየተበከሉ መምጣታቸው መሆኑን ጠቁመው ከፍተኛ ትኩረት ተሰጥቶ ሊሰራ ይገባል ብለዋል፡፡

ሻላና አብጃታ ሐይቆችም ጨዋማ እየሆኑ በመምጣታቸው ምክንያት የነበሩት የተለያዩ  የአሳ ዝርያዎች እየወደሙ መሆኑ፣ ለዚህም ምክንያቶቹ የተፋሰሱ መራቆት፣ የሐይቆቹ በአልጌ መሸፈንና በውሃ ውስጥ የኦክስጅን መጥፋት ለብዝሃ-ህይወቱ መጥፋት ምክንያት መሆኑ፣ የቆሻሻ ክምችት፣ ሐይቆቹ ከመጠን ባለፈ ሁኔታ ለመስኖና ለኢዱስትሪ እየተሳቡና እየተነኑ በመሆኑ አገሪቱ አሳሳቢ ደረጃ ላይ ደርሳለች በማለት ሀሳባቸውን አንስተዋል፡፡

ሳይንሳዊ የሆነ የውሃ አጠቃቀም ዘዴን ልንከተል እንደሚገባ፣ የህግ ማእቀፎቻችንንም ተግባራዊ ልናደርግና የተቀናጀ የውሃ ሃብት ማስተዳደር ስርዓትን መከተል እንዳለብን ያስገነዘቡት አቶ አንዱአለም በአገራችን ካሉት 12 ተፋሰሶች አንዱ የሆነው የስምጥ ሸለቆ ሐይቆች ተፋሰስ ወደ 53 ሺ ስኩዌር ኪሎ ሜትር ስፋት እንዳለውና ከእነዚህም ውስጥ ዋና ዋናዎቹ የዝዋይ-ሻላ፣ የሐዋሳ፣ የአባያ-ጫሞ እና የጨው ባህር ንዑስ ተፋሰሶች የሚጠቀሱ እንደሆኑ አንስተው ሁሉም ባለድርሻ አካላት ከተጋረጠባቸው የመድረቅ አደጋ ለመታደግ ሊረባረቡ ይገባል በማለት አሳስበዋል፡፡

ቋሚ ኮሚቴው በበኩሉ ሐይቆቹን በአካል ተንቀሳቅሶ ከተመለከተ በኋላ በሰጠው አስተያየት እንዳለው ለሐይቆቹ መበከልና የውሃ መጠን በአስደንጋጭ ሁኔታ መቀነስ ምክንያቱ ከአየር መዛባቱ ይልቅ የዜጎች የተቆርቋሪነት ማነስና በተለይም ቆሻሻን ሆንብሎ ወደ ሃይቆቹ መልቀቅ፣ ከመጠን ባለፈ ሁኔታ ለመስኖና ለኢንዱስትሪ መጠቀም የሃላፊነት መጓደል ብቻ ሳይሆን የተፈጥሮ ሚዛንንም ማዛባት በመሆኑ መንግስትና ሌሎች ባለድርሻ አካላት ሀይቆቹን መታደግ ለነገ የማይባል ተግባር እንደሆነ አውቀው ሊረባረቡ ይገባል ሲል አሳስቧል፡፡