null Wolayta Sodo University told the House that its Hospital is suffering from lack of class to give quality services.

 ወላይታ ሶዶ ዩኒቨርሲቲ ሆስፕታል ጥራት ያለው አገልግሎት ለመስጠት በክፍል ዕጥረት መቸገሩን ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አስታወቀ፡፡

በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የሴቶች፣ ወጣቶችና ማህበራዊ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ የወላይታ ሶዶ ዩኒቨርሲቲ ማስተማሪያና ሪፌራል ሆስፕታል ባለ የሙያተኛ ሁኔታ፣ የመድሃኒት አቅርቦትና ስርጭት፣ የደም ባንክ አገልግሎትና በቂ ስለመሆኑ፣ የህክምና መሳሪያዎችና መገልገያዎች አቅርቦትና ተዛማጅ ጉዳዮችን ለመመልከት ሚያዚያ 10 ቀን 2011 ዓ.ም በሆስፕታሉ የመስክ ምልከታ አድርጓል፡፡

ያለበቂ ማስፋፊያ ስራ አንድ ክፍለ ዘመን ለማስቆጠር ጥቂት ዓመታት ብቻ የቀረው ይህ ሆስፕታል የተሻለ የባለሙያ አቅምና ስብጥር እንዳለው የታየ ሲሆን በየቀኑ ከ450 እስከ 700 ለሚሆኑ ህሙማን አገልግሎት ሲሰጥ በየቀኑም ከ20 እስከ 40 ለሚደርሱ ነፍሰ ጡር እናቶች የማዋለድ አገልግሎት ይሰጣል፡፡ በቀዶ ህክምናም ያለቀጠሮ ህሙማንን የሚያስተናግድበት ሁኔታ መድረሱም ታይቷል፡፡

ሆስፕታሉ በወላይታ ዞን ለሚኖሩ ከ4 ሚሊዮን በላይ ህዝብ አገልግሎት የሚሰጥ ሲሆን ከአጎራባች 6 ዞኖች በሪፌር የሚላኩ ህሙማንንም ተቀብሎ እንደሚያስተናግድ በጉብኝቱ ወቅት ተገልጿል፡፡ ከዚህ ባሻገር የዩኒቨርሲቲው ማስተማሪያ ሆስፕታል በመሆኑ በአገልግሎት ፈላጊው እጅግ የተጨናነቀ ሆስፕታል መሆኑ ታይቷል፡፡ ቺፍ ክሊኒካል ዳይሬክተሩ ዶ/ር ሉቃስ ድንጋቶ ይህ የክፍል ዕጥረት በሁለትና ሶስት ክፍሎች አገልግሎት ማግኘት ያለባቸው ህሙማን በአንድ ክፍል እንዲስተናገዱ በማስገደዱ በአገልግሎት ጥራት ላይ የራሱን አሉታዊ ጫና ማሳደሩን ለምክር ቤቱ አባላት አስረድተዋል፡፡

ሆስፕታሉ በዩኒቨርሲቲ ስር መተዳደር ከጀመረ ወዲህ የገንዘብ ዕጥረት ባይኖረውም በኢትዮጵያ መድሃኒት ፈንድ አቅርቦት ኤጀንሲ በኩል የሚቀርበው የመድሃኒት አቅርቦት የሆስፕታሉን 31 በመቶ ብቻ ፍላጎት ስለሚሸፍን መሰረታዊ መድሃኒቶችን እንኳን ለህሙማን ለማቅረብ ያለመቻሉን ዶ/ር ሉቃስ እንደችግር አንስተዋል፡፡ በራስ ገንዘብም ከ200,000 ብር በላይ መድሃኒት እንዳይገዛ ገደብ መቀመጡና ከግል መድሃኒት ተቋማትም መድሃኒት ለህሙማን ለማቅረብ በኦዲት ተቋማት በኩል እንደኦዲት ግኝት እየተወሰደ ህሙማንን ለመታደግ መቸገራቸውን ዶ/ር ሉቃስ ለኮሚቴው አባላት አስረድተዋል፡፡ ስምንት ሚሊዮን ብር የህክምና መገልገያ መሳሪያ ለመግዛት ለኤጀንሲው ገቢ ቢደርጉም እስከአሁን ድረስ መሳሪያዎቹ ባለመቅረባቸው በመድሃኒት እና የህክምና መገልገያ መሳሪያዎች አቅርቦት በኩል ኤጀንሲው ሃላፊነቱን እየተወጣ ያለመሆኑን ዶክተር ሉቃስ እንደችግር አንስተዋል፡፡

በደም ባንክ በኩልም በዞኑ የደም ባንክ ጣቢያ ቢቋቋምም በበጀት፣ በቁሳቁስና በተሽከርካሪ ዕጦት የተፈለገውን ደም ስለማይሰበስብ በየሳምንቱ ከአዲስ አበባ 100 ዩኒት ሆስፕታሉ እንደሚያስመጣ የተገለፀ ሲሆን በደም ዕጦት የአንዲት እናት ህይወት ማለፉም ታውቋል፡፡ ከዚህ ሌላ ሪፌር የሚያደርጉ አጎራባች ሆስፕታሎችም በእጃቸው የተጎዱ እናቶችን ስለሚልኩ በመዘገየት ምክንያት ባለፉት 9 ወራት የ5 እናቶች ሞት መከሰቱም ተገልጿል፡፡ ዶክተር ሉቃስ ሆስፕታሎቹ በሞት አፋፍ ያሉ እናቶችን በአካባቢያቸው አንድም እናት በወልድ ምክንያት አልሞተችም ለማለት ወደሆስፕታሉ ስለሚልኩ ይህም የሆስፕታሉ ሌላው ችግር መሆኑንም ጠቁመዋል፡፡

የቡድኑ አስተባባሪ የተከበሩ አቶ ሙላጎ ሻፊ የሆስፕታሉ አገልግሎት አሰጣጥ ጥሩ መሆኑን ጠቁመው ለአገልግሎት ጥራት ፈተና የሆነውን የክፍል ጥበት ለመቅረፍ ጉዳዩን ለሚመለከታቸው አካላት ኮሚቴው እንደሚያቀርብ ቃል ገብተዋል፡፡

አንድ የሆስፕታሉ የስራ ባልደረባ በሰጡት አስተያየት የመንግስት ሃላፊዎች ይህን ሆስፕታል በተደጋጋሚ እየጎበኙ ችግሩን ለመፍታት ቃል ቢገቡም የተገኘ ውጤት የለም ብለዋል፡፡

ቺፍ ክሊኒካል ዳይሬክተሩ ዶክተር ሉቃስ ድንጋቶ የክፍል ዕጥረቱ የሚፈታበትና እና ገዳቢ አሰራሮች የሚሻሻሉበት ሁኔታ ላይ ቋሚ ኮሚቴው ትኩረት ሰጥቶ እንዲሰራ ጥያቄ አቅርበዋል፡፡