(ዜና ፓርላማ)፤ ጥር 16፣ 2015 ዓ.ም፤ ምክር ቤቱ ዛሬ ባካሄደው 9ኛ መደበኛ ስብሰባው ስድስት ረቂቅ አዋጆችን እና አንድ ደንብን ለዝርዝር ዕይታ ለሚመለከታቸው ቋሚ ኮሚቴዎች መርቷል።

በረቂቅ አዋጆቹ አስፈላጊነት ላይ የመንግስት ረዳት ተጠሪ ሚንስትር ዴኤታ የተከበሩ ወ/ሮ መሰረት ኃይሌ ለምክር ቤቱ ማብራሪያ አቅርበዋል፡፡

ረቂቅ አዋጆቹን አስመልክቶ የምክር ቤት አባላት የሚመሩላቸው ቋሚ ኮሚቴዎች ቢመለከቷቸው ያሏቸውን አስተያየቶችንም አቅርበዋል፡፡

የምክር ቤቱ አፈ-ጉባኤ የተከበሩ አቶ ታገሰ ጫፎ ረቂቅ አዋጆቹን እና ደንቡን በተመለከተ ከምክር ቤት አባላት የተነሱ አስተያየቶችን የሚመራላቸው ቋሚ ኮሚቴዎች በየደረጃው በሚያካሂዷቸው ውይይቶች እንዲመለከቷቸው አሳስበዋል፡፡

ምክር ቤቱም ረቂቅ አዋጆቹን እና ደንቡን የሚመለከታቸው ቋሚ ኮሚቴዎች እንዲመረምሯቸው በሙሉና በአብላጫ ድምጽ በመምራት የዕለቱን ጉባኤ አጠናቋል፡፡

ለየቋሚ ኮሚቴዎች የተመሩ ረቂቅ አዋጆች እና ደንብም በኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ መንግስት እና በዓለም አቀፍ የልማት ማህበር መካከል ለሁለተኛው ምዕራፍ የዘላቂ መሬት አያያዝ ፕሮጀክት ማስፈጻሚ የተደረገውን የብድር ስምምነት ለማፅደቅ የቀረበ ረቂቅ አዋጅ፤ አዋጅ ቁጥር 10/2015 ሆኖ ለዝርዝር ዕይታ ለፕላን፣ በጀትና ፋይናንስ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ በሁለት ድምጸ ተዓቅቦ በአብላጫ ድምጽ ተመርቷል፡፡

የኤክሳይዝ ታክስ አዋጅን ለማሻሻል የቀረበ ረቂቅ አዋጅ፤ ረቂቅ አዋጅ ቁጥር 11/2015 ሆኖ ለዝርዝር ዕይታ ለፕላን፣ በጀትና ፋይናንስ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ በሙሉ ድምጽ ተመርቷል፡፡

በኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ መንግስት እና በቱርክ ሪፐብሊክ መንግስት መካከል የተደረገውን የአሳልፎ መስጠት ስምምነት ለማፅደቅ የቀረበ ረቂቅ አዋጅ፤ ረቂቅ አዋጅ ቁጥር 12/2015 ሆኖ ለዝርዝር ዕይታ ለህግና ፍትህ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ በአንድ ድምፀ ተዓቅቦ በአብላጫ ድምጽ ተመርቷል፡፡

በኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ መንግስት እና በቱርክ ሪፐብሊክ መንግስት መካከል የተደረገውን በወንጀል ጉዳዮች የጋራ የህግ ትብብር ስምምነት ለማፅደቅ የቀረበ ረቂቅ አዋጅ፤ ረቂቅ አዋጅ ቁጥር 13/2015 ሆኖ ለዝርዝር ዕይታ ለህግና ፍትህ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ በአንድ ድምፀ ተዓቅቦ በአብላጫ ድምጽ ተመርቷል፡፡

በኢትዮጵያ ፌደራላዊ ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ መንግስት እና በተባበሩት አረብ ኤሜሬቶች መንግስት መካከል የተደረገውን በወንጀል ጉዳዮች የጋራ የህግ ትብብር ስምምነት ለማፅደቅ የቀረበ ረቂቅ አዋጅ፤ ረቂቅ አዋጅ ቁጥር 14/2015 ሆኖ ለዝርዝር ዕይታ ለህግና ፍትህ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ በሙሉ ድምጽ ተመርቷል፡፡

በኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ መንግስት እና በተባበሩት አረብ ኤሜሬቶች መንግስት መካከል የተደረገውን የአሳልፎ መስጠት ትብብር ስምምነት ለማፅደቅ የቀረበ ረቂቅ አዋጅ፤ ረቂቅ አዋጅ ቁጥር 15/2015 ሆኖ ለዝርዝር ዕይታ ለህግና ፍትህ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ በሙሉ ድምጽ ተመርቷል፡፡

የፌደራል ፍርድ ቤቶች ሰራተኞች ደንብ ቁጥር 1/2015 ሆኖ ለዝርዝር ዕይታ በዋነኛነት ለህግና ፍትህ፣ በተባባሪነት ለሰው ኃብት ልማት፣ ስራ ስምሪትና ቴክኖሎጂ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴዎች በሙሉ ድምጽ ተመርቷል።

በ ኃ/ሚካኤል አረጋኸኝ

ተጨማሪ መረጃዎችን ለማግኘት

በፌስቡክ http://www.facebook.com/hoprparliament

በዩቲዩብ https://www.youtube.com/@FDREHOPR

በቴሌግራም https://t.me/ParlamaNews

በትዊተር http://twitter.com/fdrehopr

በዌብሳይት www.hopr.gov.et ይከታተሉ