የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ጽ/ቤት የስራ ኃላፊዎች በሁለት ረቂቅ ሰነዶች ላይ ተወያዩ 

(ዜና ፓርላማ)፣ ግንቦት 14 ቀን 2013 ዓ.ም. የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ጽ/ቤት የስራ ኃላፊዎች በአገልግሎት አሰጣጥ መምሪያ እና በፓርላማ መረጃ መጽሐፍ ረቂቅ ሰነዶች ላይ በቢሸፍቱ ሁለት ቀን የፈጀ ውይይት አካሂደዋል።

ውይይቱን የመሩት የምክር ቤቱ ጽ/ቤት ዋና ጸሐፊ ዶ/ር ምስራቅ መኮንን በአገልግሎት አሰጣጥ መምሪያ ረቂቅ ሰነዱ ላይ የተካሄደውን ውይይት ሲያጠቃልሉ እንዳሉት የሰነዱ ዓላማ ተገልጋዮች አገልግሎቱን የት፣ ከማን፣ እንዴትና መቸ እንደሚያገኙ እና አገልግሎት አሰጣጡን ማቀላጠፍ በመሆኑ በዚሁ መንገድ ተስተካክሎ በ15 ቀን ውስጥ ማድረስ አለበት ብለዋል።

ሁለቱ ምክትል ዋና ጸሐፊዎችም ሰነዱን በየዘርፎቻቸው በድጋሚ አይተው የስራ ቅብብሎሹን በሚያሳይ መንገድ እንዲዘጋጅ ማድረግ ይጠበቅባቸዋል ሲሉም አክለዋል።

ሰነዱን ያዘጋጁት ኮሚቴዎች በበኩላቸው የተሰጠውን አስተያየት በግብአትነት ወሰደው የተደራጀ ሰነድ እንደሚያዘጋጁ  ገልጸው ነገር ግን በሰነዱ ላይ እንዲካተቱ የተፈለገው ዋና ዋና ጉዳዮች ዝርዝር ተግባራት አለመሆናቸውን አስረድተዋል።

በሁለተኛ ደረጃ ለውይይት የቀረበው የፓርላማ መረጃ መጽሐፍ ረቂቅ ሰነድ ሲሆን በተሳታፊዎች በርካታ የማስተካከያ ሃሳቦቸች ተነስተው ውይይት ከተደረገ በኋላ ሰነዱ አጠር ብሎ ታሪክ ሳይበዛበት ለአጠቃቀም በሚመች መንገድ መዘጋጀት እንዳለበት ተመላክቷል።

የጽ/ቤቱ ዋና ጸሐፊ ዶ/ር ምስራቅ መኮንን በበኩላቸው ሰነዱ የተዘጋጀበት ዋና አላማ አዲስ ወደ ምክር ቤቱ የሚቀላቀሉ የምክር ቤት አባላት በቀላሉ ወደ ተግባር የሚገቡበትንና ጥያቄ የሚፈጥሩባቸውን ጉዳዮች መፍታት በመሆኑ ትኩረቱን ከታሪክ መጽሐፍነት ይልቅ  በመረጃ ሰጭነት ላይ አዱርጎ መዘጋጀት አለበት ብለዋል።

ውይይት የተደረገባቸው ረቂቅ ሰነዶች ጽ/ቤቱ ባደራጃቸው ሁለት የተለያዩ ኮሚቴዎች ያላሰለሰ ጥረት ለወራት ተደክሞባቸው የቀረቡ ሲሆን አዘጋጅ ኮሚቴዎቹ ሰነዶቹን በዚህ ደረጃ አዘጋጅተው ለውይይት በማቅረባቸው በተሳታፊዎች ምስጋና ተቸሯቸዋል።