(ዜና ፓርላማ)፣ ሰኔ 4፣ 2015 ዓ.ም፤ የተጀመረው የፍትህ ተቋማት የለውጥ ፍኖተ-ካርታ ትግበራ ትኩረት ተሰጥቶ ሊሰራ እንደሚገባ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ-ጉባኤ የተከበሩ አቶ ታገሰ ጫፎ ገለጹ። 

ውጤታማ እና በሕዝብ ዘንድ ተአማኒነት ያለው የፍትህ ሥርዓትን ለማረጋገጥና ለማጠናከር በፌደራል የፍትህ ተቋማት የተጀመረው የፍትህ የለውጥ ፍኖተ-ካርታን በየደረጃው ያሉ የፍትህ ተቋማት ህብረተሰቡን በማሳተፍ ለመተግበር በትኩረት  መስራት ይገባቸዋል ብለዋል።   

በየደረጃው የሚገኙ የፍትህ ተቋማት ተቋማዊ ነፃነታቸው ተጠብቆ በሰው ኃይል እና በቴክኖሎጂ ታግዘው በመስራት የህብረተሰቡን የፍትህና የመልካም አስተዳደር ችግሮችን ለመፍታት ለፍኖተ-ካርታው ትግበራ ርብርብ ሊያደርጉ እንደሚገባም የተከበሩ አፈ-ጉባኤ አስገንዝበዋል፡

የሁሉም ክልሎች እና የደቡብ ብሔረሰቦች ምክር ቤቶች እንዲሁም የፌዴሬሽን ምክር ቤት የተሳተፉበት የሀገር አቀፍ የህግ አውጪዎች የጋራ የምክክር መድረክ የእርስ በእርስ ግንኙነትን ከማጠናከር ባሻገር መልካም ተሞክሮዎች ልውውጥ ተደርጎበታል።

በመድረኩ በፌደራል ደረጃ በፍትህ ሥርዓቱ ላይ የተጀመሩ የሪፎርም ስራዎችን በክልሎችም ለማስፋት የሚያግዝ ምክክር ተደርጓል።

በህግ አውጪዎች መካከል የሚደረገው ውይይት ዘላቂ ሰላምን በማስፈን፣ ዋስትና ያለው ዴሞክራሲን ለማረጋገጥ እና ፈጣን እድገት በማስመዝገብ አንድ የፖለቲካ ኢኮኖሚ ማህበረሰብ ለመፍጠር ፋይዳው የጎላ መሆኑንም ተገልጿል።

በሱማሌ ክልል ጅግጅጋ ከተማ ሲካሄድ የነበረው የሀገር አቀፍ የህግ አውጪዎች የጋራ የምክክር መድረክ ትናንት ማምሻውን ተጠናቋል።

ተጨማሪ መረጃዎችን ለማግኘት፡- 
በፌስቡክ http://www.facebook.com/hoprparliament 
በዩቲዩብ https://www.youtube.com/@FDREHOPR 
በቴሌግራም https://t.me/ParlamaNews 
በትዊተር http://twitter.com/fdrehopr 
በዌብሳይት www.hopr.gov.et ይከታተሉ