በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የውኃ፣ መስኖ፣ ቆላማ አካባቢ እና አካባቢ ልማት ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ባካሄደው ምልከታ፤ በሞጆ - አዳማ የውኃ አቅርቦት ፕሮጄክት መጓተት መንስዔ፣ የአዳማ ከተማ የውኃ ዕጥረት በተፈለገው ጊዜ ሊቀረፍ አለመቻሉ ተረጋገጠ፡፡

ይህ የተረጋገጠው፤ ቋሚ ኮሚቴው ሰሞኑን የሞጆ - አዳማን የውኃ አቅርቦት ፕሮጄክት የግንባታ ሂደት በአካል ተገኝቶ በጎበኘበት ወቅት ነው፡፡

ፕሮጄክቱ አዳማ በቂ የውኃ አቅርቦት እንዲኖራት ታስቦ ቢጀመርም፤ የፕሮጄክቱ ግንባታ በመጓተቱ ምክኒያት፣ የከተማዋን የውኃ ችግር በሚፈለገው ፍጥነት መቅረፍ እንዳልተቻለ ቋሚ ኮሚቴው አረጋግጧል፡፡

በውሉ መሠረት በ7 መቶ 30 ቀናት ይጠናቀቃል ተብሎ የነበረው ይህ ፕሮጄክት፤ በዲዛይን ክለሳ፣ በተቋራጮች እና በአማካሪዎች አለመግባባት፣ እንዲሁም በግንባታ ቁሳቁሶች ዋጋ መጨመር ምክኒያቶች የተጓተተ ሲሆን፤ አፈጻጸሙም ገና ከ14 በመቶ ያልዘለለ እንደሆነ ኮሚቴው ተገንዝቧል፡፡

የፕሮጄክቱ ሥራ ኃላፊነቱ በተወሰነ የቻይና ዓለም-አቀፍ የግንባታ ኩባኒያ (CGCOC Group Co., Ltd.) የሚካሄድ ሲሆን፤ የአዳማ ከተማን የውኃ ችግር ለአንዴ እና ለመጨረሻ ጊዜ ይፈታል የሚል ተስፋ የተጣለበት ነበር፡፡ ለዚህም፤ ሞጆ ከባቢ 15 ጥልቅ የውኃ ጉድጓዶች እንዲቆፈሩ ዕቅድ ተይዞ፣ እስከአሁን ሁለት ጉድጓዶች ብቻ መቆፈራቸውን ኮሚቴው አረጋግጧል፡፡

የቋሚ ኮሚቴው አባል የተከበሩ አቶ መስፍን ዳኜ፤ የውኃ ችግር ይደር የማይባል ጉዳይ መሆኑ ታውቆ፣ የፕሮጄክቱ ሥራ መፋጠን አለበት ብለዋል፡፡ የአዳማ ከተማ ሕዝብም ከዚህ አስከፊ ችግር እንዲላቀቅ፤ በየደረጃው ርብርብ ሊደረግበት ይገባል - የተከበሩ መስፍን እንደጠቆሙት፡፡

“የፕሮጄክቱ ሥራ አሳማኝ ባልሆኑ ምክኒያቶች መዘግየት የለበትም፡፡ ፕሮጄክቱ በአስቸኳይ እንዲጠናቀቅ እና የከተማዋ ሕዝብም ከውኃ ችግር እንዲላቀቅ፤ በየደረጃው የሚገኙ አመራሮች በትኩረት መንቀሳቀስ ይኖርባቸዋል” የተከበሩ መስፍን እንዳሉት፡፡

ፕሮጄክቱ ያላሳለሰ ጥረት ተደርጎበት፣ በአጭር ጊዜ ተጠናቅቆ የሕዝቡ ተጠቃሚነት እንዲረጋገጥ ያመላከቱት ደግሞ፤ ሌላኛው የኮሚቴው አባል የተከበሩ አቶ ኢብሳ የሱፍ ናቸው፡፡ የሚመለከታቸው የመንግስት አካላት ሁሉ ለፕሮጄክቱ የተሳካ አፈጻጸም ልዩ ትኩረት እንዲሰጡም፤ የተከበሩ ኢብሳ አያይዘው አሳስበዋል፡፡

አዳማን ውብ እና ጽዱ ከተማ ለማድረግ የሚፈስሰውን ጥረት እና መልካም ጅማሮ የሚታይበትን የደረቅ ቆሻሻ አወጋገድ ሥርዓት፤ ቋሚ ኮሚቴው በበጎ አይቷል፡፡ የፕላስቲክ ጠርሙሶች ተመልሰው አገልግሎት እንዲሰጡ መሠራቱንም እሰዬው ብሏል፡፡ በፕላስቲክ ፌስታል ልየታ በኩል ግን ክፍተት እንዳለ ተመልክቷል፡፡

በተያያዘ ዜናም፤ ኮሚቴው የአዳማ ከተማ የፈሳሽ ቆሻሻ ማጣሪያ ፕሮጄክት ግንባታ እንዲጀመር በ2012 ዓ.ም. የመሠረት ድንጋይ ይጣል እንጂ፤ እስካሁን ድረስ በዲዛይን እና ተያያዥ ችግሮች መንስዔነት፤ ግንባታው መጓተቱን በስፍራው ተገኝቶ አረጋግጧል፡፡

የአዳማ ከተማ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ ክቡር መሐመድ ጉዬ፤ አዳማ ከተማ በዕድገት ግስጋሴ ብትሆንም ውኃን ጨምሮ አንዳንድ አስፈላጊ መሠረተ-ልማቶች ገና ተደራሽ አለመሆናቸውን ገልጸዋል፡፡ በተለይም የከተማዋን የውኃ ችግር እስካሁንም መቅረፍ እንዳልተቻለ ለቋሚ ኮሚቴው ገልጸዋል፡፡

የውኃ ፕሮጄክቱን ሥራ ያጓተቱትን ችግሮች ለመፍታት በየዘርፉ ጥረት ቢደረግም፤ የፕሮጄክቱ ግንባታ አፈጻጸም አጥጋቢ ሊሆን አለመቻሉን፣ ምክትል ከንቲባው አክለው ተናግረዋል፡፡

ከተማዋን ለማስዋብ በሕብረተሰቡ ተሳትፎ ዘርፈ-ብዙ ሥራዎች እየተከናወኑ እንደሆነ የገለጹት ክቡር መሐመድ፤ አሁን ያለው የደረቅ ቆሻሻ አወጋገድ ሥርዓት ከተማዋን የማይመጥን እንደሆነ ተገንዝበን፣ የተሻለ ቆሻሻ ማስወገጃ እንዲኖር እየሠራን ነው ብለዋል፡፡

በአዳማ ከተማ አስተዳደር የመጠጥ ውኃ እና ፈሳሽ አገልግሎት ድርጅት ጽሕፈት ቤት ቡድን መሪ አቶ ካሣ በኩረ በበኩላቸው፤ በከተማዋ 24 የሕዝብ እና የጋራ መጸዳጃ ቤቶችን ለመገንባት ታቅዶ፣ 18ቱ ግንባታቸው ተጠናቅቆ ርክክብ መደረጉን ገልጸዋል፡፡ የቀሩት ስድስቱ ደግሞ በቦታ እጦት ምክኒያት ግንባታቸው እንዳልተካሄደ አያይዘው አስረድተዋል፡፡