ኢትዮጵያ የኢንቨስትመንት አድማሷን ለማስፋት ከአርጀንቲና ጋር በትብብር እንደምትሰራ ተገለጸ

(ዜና ፓርላማ)፣ መጋቢት 08/2013 ዓ.ም.፤ አዲስ አበባ፤ ኢትዮጵያ የተለያዩ የኢንቨስትመንት አማራጮችን ለማስፋት ከአርጀንቲና ጋር በትብብር እንደምትሰራ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የውጭ ግንኙነት እና የሰላም ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ የተከበሩ ነገሪ ሌንጮ (ዶ/ር) ገለጹ፡፡

ሰብሳቢው ይህንን የገለጹት በኢትዮጵያ የአርጀንቲና አምባሳደር ጉስታቮ ቴዎድሮ የተመራው ልዑክን በጽ/ቤታቸው ተቀብለው ባነጋገሩበት ወቅት ነው፡፡

ኢትዮጵያ ከአርጀንቲና ጋር የሁለትዮሽ ግንኙነቷን በማጠናከር በንግድ፣ በኢንቨስትመንት፣ በሳይንስና ቴክኖሎጂ፣ በሰፖርት፣ በቱሪዝም እና በኪነ-ጥበቡ ዘርፍ በትብብር እንደምትሰራ ነው ነገሪ (ዶ/ር ) ለአምባሳደሩ ያብራሩላቸው፡፡

የተለያዩ ውስጣዊ እና ውጫዊ ፈተናዎችን በመጋፈጥ ኢትዮጵያ ፈጣን የኢኮኖሚ ዕድገት እያስመዘገበች እንደምትገኝ የገለጹት ሰብሳቢው፣ ዕድገቱ ዘላቂ እንዲሆን የታዳሽ ሃይል ተሞክሮን ከአርጀንቲና በመውሰድ የአረንጓዴ ልማት ዘርፉንም ጭምር ለማሳደግ በትኩረት እንደሚሰራ ተናግረዋል፡፡

የሁለቱ ሃገራት የሁለትሽ ግንኙነት በኢንቨስትመንትና በንግዱ ዘርፍ ሳይገደብ የሚዲያ እና ተግባቦት መሳሪያዎችን በመጠቀም በሃገራቱ የግብርና እና የባሕል ዘርፉ ላይም ትኩረት እንደሚደረግ ነገሪ ( ዶ/ር ) ጠቅሰዋል፡፡

በትግራይ ክልል የተወሰደውን የሕግ ማስከበር እርምጃን የገለጹት ሰብሳቢው የፌዴራል መንግስት ለሕወሓት የዕርቅ እና የይቅርታ በሮቹን የከፈተ ቢሆንም  የመንግስትን ሃሳብ ውድቅ በማድረግ የፌዴራል መንግስቱን በማጥቃቱ መንግስት ተገድዶ ሕግ ወደ ማስከበር እርምጃ እንዲገባ ማድረጉን ለአምባሳደሩ ገልጸውላቸዋል፡፡

ይሁን እንጂ የውስጥ ሃይሎች ከውጭ ሃይሎች ጋር በመቀናጀት ጤናማ ያልሆነ የፖለቲካ ትርፍ ለማግኘት ሲሉ የፌዴራል መንግስቱ በትግራይ ክልል የሰብዓዊ መብት ጥሰት እንደፈጸመ  አድርገው  የተሳሳተ መረጃ እያሰራጩ እንደሚገኙ ያስረዱት ነገሪ (ዶ/ር) ኢትዮጵያ የየትኛውንም ሃገር አላስፈላጊ ጣልቃ-ገብነት እንደማታስተናግድም አክለው ጠቅሰዋል ፡፡

አምባሳደር ጉስታቮ ቴዎድሮ በበኩላቸው፣ አርጀንቲና በኢንቨስትመንት፣ በንግድ፣ በትምህርት፣ በግብርና እና በታዳሽ ሃይል ዙሪያ ከኢትዮጵያ ጋር በትብብር ለመስራት ፍላጎት እንዳላት ገልጸዋል፡፡

የኢንቨስትመንት ዘርፉን ለማስፋት የአርጀንቲና ባለሃብቶች ወደ ኢትዮጵያ እንደሚመጡ አምባሳደሩ ተናግረዋል፡፡

የንግድ ዘርፉ የተቀላጠፈ እንዲሆን የኢትዮጵያ አየር መንገድ ወደ አርጀንቲና የሚበርበትን ቀናት ለመጨመር ከሃገራቸው መንግስት ጋር መምከራቸውን እና በሳምንት ሶስት ቀን እንዲበር ቃል እንደተገባላቸው አምባሳደሩ ጠቅሰዋል፡፡

ሃገራቸው በሕግ ማስከበር ዘመቻው ጉዳት ለደረሰባቸው የሕብረተሰብ ክፍሎች የሰብአዊ እርዳታ ለማድረግ የሀገራቸው መንግስት ፍላጎት እንዳለው ገልጸው፣ የኢትዮጵያ የውስጥ ጉዳይ የኢትዮጵያዊያን መሆኑን  አምባሳደር ጉስታቮ ተናግረዋል፡፡

የሮማው ሊቀ ዻዻስ ፖፕ ፍራንሲስ ለኢትዮጵያ እና ኢትዮጵያዊያን የተለየ አድናቆት እንዳለቸው እንደገለጹላቸው እና ኢትዮጵያን ለመጎብኘት በቅርቡ እንደሚመጡ  ነግረውኛል ሲሉም አምባሳደር ጉስታቮ ተናግረዋል፡፡

በሕግ ማስከበር ዘመቻ ጉዳት ለደረሰባቸው ወገኖች አርጀንቲና የሰብዓዊ ድጋፍ ለማድረግ ላሳየችው  ፍላጎት ነገሪ ( ዶ/ር ) ምስጋናቸውን  አቅርበዋል፡፡

ዘጋቢ፣ ስሜነው ሲፋረድ