ከሲዳማ ክልል የተመረጡ የሕዝብ ተወካዮች ም/ቤት አባላት ክልሉ የኑሮ ውድነትና የስራ አጥነት ችግር ለመፍታት ትኩረት ሰጥቶ መስራት እንዳለበት ገልጸዋል፡፡

የም/ቤት አባላቱ ይህን የገለጹት በየደረጃው ካሉ የክልሉ አመራሮች ጋር በተወያዩበት ወቅት ነው፡፡

የተከበሩ አቶ ሰለሞን ላሌ የቡድኑ አስተባባሪና በህዝብ ተወካዮች ም/ቤት የግብርና ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ እና በም/ቤቱ የፕላን፣ በጀትና ፋይናንስ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ አባል የተከበሩ አቶ አኔሳ ማልኮ ሕዝቡ ካነሳው በርካታ ጥያቄዎች መካከል የኑሮ ውድነት፣ ለወጣቶች ሥራ ዕድል የመፍጠር ጉዳይ፣ የምርጥ ዘርና ማዳበሪያ አቅርቦት፣ የዋጋ ንረትና የመብራት መቆራረጥ ችግሮችን የክልሉ መንግሥት አፅንዖት ሰጥቶ እንዲፈታላቸው አሳስበዋል፡፡

አያይዘውም በክልሉ በርካታ ተጀምረው ያልተጠናቀቁ የመንገድ ፕሮጀክቶች እንዳሉና የውሃ፣ የጤና አገልግሎት፣ የትምህርት ጥራት በአግባቡ እንዲመለሱና የህዝብን ሀብት በሚያባክኑ ሌባና ብልሹ አሠራር በሚፈፅሙ አመራሮች ላይ የክልሉ መንግሥት አስተማሪና ሕጋዊ እርምጃ ሊወሰድ ይገባል ሲሉም ተናግረዋል።

የክልሉ ፕሬዘደንት ክቡር አቶ ደስታ ሌዳሞም በምክር ቤት አባላቱ የተሰጠን ግብረ መልስ የሚጠቅመን ነው በማለት አመስግነው እንደ ሀገር የገጠመንን የኑሮ ውድነትና የወጣቱን የሥራ ዕድል ፈጠራ ጥያቄ ለመመለስ የሕዝብ ንቅናቄ መድረኮችን በመፍጠር የጋራ ግንዛቤ የማሳደግ ሥራ እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

አክለውም በክልሉ ደረጃ የምንሠራቸውን የልማት ጥያቄዎች የገቢ አቅም በፈቀደ መጠን ነባር ፕሮጄክቶችን በማስቀደም እንደሚሠራና የሕዝቡን ተጠቃሚነት የሚጎዱ ሌብነትንና ብልሹ አሠራርን ለማስወገድ እንሰራለን ብለዋል።