አዋጁ የሀገሪቱን የድጎማና የጋራ ገቢዎች ክፍፍል ግልጸኝነትና ፍትሃዊነትን የሚያረጋግጥ መሆኑ ተጠቆመ

(ዜና ፓርላማ) ሰኔ 3 ቀን 2013 ዓ.ም.፣ አዲስ አበባ፤ አዋጁ የሀገሪቱን የድጎማና የጋራ ገቢዎች ክፍፍል ግልጸኝነትና ፍትሃዊነትን የሚያረጋግጥ መሆኑ የተጠቆመው የኢፌዴሪ የህዝብ ተወካዮች ም/ቤት ዛሬ ባካሄደው 14ኛ መደበኛ ጉባኤው የፌደራል ድጎማ በጀትና የጋራ ገቢዎች ክፍፍል ስርዓትና ተቋማዊ አደረጃጀትን ለመወሰን በወጣ ረቂቅ አዋጅ ላይ በተወያየበት ወቅት ነው፡፡

የረቂቅ አዋጁን ሪፖርትና የውሳኔ ሀሳብ ለም/ቤቱ ያቀረቡት የህግ፣ ፍትህና ዴሞክራሲ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ የተከበሩ አቶ አቡ ብርኪ ሲሆኑ የፌደራል መንግስቱ የድጎማ በጀትንም ሆነ የጋራ ገቢዎች ለክልሎች የሚከፋፈልበት መንገድ ወጥነትና ቅንጅት የጎደለው በመሆኑ ክፍፍሉ ሚዛናዊና ውጤታማነት ላይ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተስተዋሉ የመጡ ክፍተቶችን ለመቅረፍና መደበኛና የተቀናጀ አሰራርን መዘርጋትና ተግባራዊ ማድረግ ይቻል ዘንድ አዋጁን ማሻሻል ማስፈለጉን ለም/ቤቱ አብራርተዋል፡፡

በረቂቅ አዋጁ ላይ በርካታ ማሻሻያዎች የተደረጉ መሆኑን ያመለከቱት የቋሚ ኮሚቴው ሰብሳቢ ተቋማዊ አደረጃጃት የሚለው ሀረግ በረቂቅ አዋጁ ኮሚሽን ለማቋቋም የታሰበው ባለማስፈለጉና ተግባሩንም የፌዴሬሽን ም/ቤት ጽ/ቤት የሚያከናውነው በመሆኑ ሙሉ በሙሉ እንዲወጣ መደረጉንና ኮሚሽን በሚለው ቦታ የፌዴሬሽን ም/ቤት ጽ/ቤት በሚለው ሙሉ በሙሉ መተካቱን ገልጸዋል፡፡

ስለሆነም የቀረበው ረቂቅ አዋጅ በሀገሪቱ የድጎማ በጀት እና የጋራ ገቢዎች ክፍፍል የተሻለና የጋራ ሀብትን በግልጽ ተጠቃሚ የሚያደርግ፣ ግልጸኝነትና ፍትሀዊነትን የሚያረጋግጥ አሰራር እንዲኖር የሚያደርግ በመሆኑ ም/ቤቱ እንዲያፀድቀው ነው የውሳኔ ሀሳቡን ያቀረቡት፡፡

ከም/ቤት አባላት ረቂቅ አዋጁ ምክር ቤቱ ህዳር 4 ቀን 2012 ዓ.ም ባካሄደው መደበኛ ስብሰባው በዋነኛነት ለህግ፣ ፍትህና ዴሞክራሲ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ እና በተባባሪነት ለገቢ፣ በጀትና ፋይናንስ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴዎች የመራው በመሆኑ አልዘገየም ወይ? ረቂቅ አዋጁን ከነማሻሻያው ለመቀበል በኮሚቴው አባላት የልዩነት ሀሳብ ተነስቷል ተብሏልና የልዩነት ሀሳቦቹ ምን ነበሩ? የሚሉት ጥያቄዎች በዋነኛነት ተነስተዋል፡፡

ምላሽ የሰጡት የቋሚ ኮሚቴው ሰብሳቢ የተከበሩ አቶ አቡ ብርኪ ረቂቅ አዋጁ መዘግየቱን ጠቁመው የዘገየበት ዋነኛ ምክንያት በሀገሪቱ በተከሰተው የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝና የልዩነት ሃሳቡም የመጣው ኮሚሽኑ ይኑር አይኑር በሚል መሆኑን አብራርተዋል፡፡

ም/ቤቱ በረቂቅ አዋጁ ላይ በስፋት ከጀወያየ በኋላ የፌደራል ድጎማ በጀትና የጋራ ገቢዎች ክፍፍል ስርዓትና ተቋማዊ አደረጃጀትን ለመወሰን የቀረበው ረቂቅ አዋጁ አዋጅ ቁጥር 1250/2013 ዓ.ም ሆኖ በ2 ተቃውሞና በ1 ድምጸ ተዓቅቦ በአብላጫ ድምጽ አፅድቆታል፡፡

በኃ/ሚካኤል አረጋኽኝ