(ዜና ፓርላማ)፤ ታህሳስ 20፣ 2014 ዓ.ም.፣ አዲስ አበባ፤ የኢፌዴሪ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ባካሄደው ሁለተኛ ልዩ ስብሰባው፤ ሀገራዊ የምክክር ኮሚሽን ለማቋቋም የቀረበውን ረቂቅ አዋጅ በአብላጫ ድምጽ አጸደቀ፡፡

በዚሁ ወቅት የምክር ቤቱ አፈ-ጉባዔ የተከበሩ አቶ ታገሠ ጫፎ፤ ተጠሪነቱ ለምክር ቤቱ የሆነው ይህ ኮሚሽን ሥራውን ገለልተኛ እና ተዓማኒ እንዲሁም አካታች በሆነ መልኩ መሥራት እንዳለበት አሳስበዋል፡፡

ክቡር አፈ-ጉባዔው አያይዘውም፤ በሀገራዊ ጉዳዮች ሀገራዊ እና ተቀራራቢ አመለካከት ለመያዝ ከሚያበቁ ተቋማት አንዱ ይህ ኮሚሽን መሆኑንም አስገንዝበዋል፡፡

የሕግ፣ ፍትሕ እና ዴሞክራሲ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ የተከበሩ ወ/ሮ እፀገነት መንግስቱ ረቂቅ አዋጁ ለዝርዝር እይታ ከተመራበት ጊዜ አንስቶ የአዋጁን ክብደት ከግምት በማስገባት ይፋዊ የህዝብ ውይይት ሲደረግበት እንደቆየ ገልጸዋል፡፡

በዚህም የፍትህ አካላት፣ የሲቪክ ማህበራት፣ የኢትዮጵያ የኃይማኖት ጉባኤ፣ የመንግስት እና የግል ሚዲያ ተቋማት፣ የዩኒቨርስቲ ምሁራን፣ ታዋቂ ግለሰቦች የተሳተፉ ሲሆን፤ በተጨማሪም ከክልል እና ከተማ አስተዳደሮች የሚመለከታቸውን አካላት በማሳተፍ አዋጁን ለማዳበር የሚያስችሉ ግብዓቶች መገኘታቸውንም አብራርተዋል፡፡

የተከበሩ ወ/ሮ እፀገነት አክለውም፤ ቋሚ ኮሚቴው በምርመራው ወቅት ያገኛቸውን ጭብጦች ያብራሩ ሲሆን፤ የሀገራዊ ምክክር ኮሚሽኑን የሚመሩ አካላት ብቃት እና ገለልተኝነት ያላቸው መሆን እንደሚገባቸው አመላክተዋል፡፡

የኮሚሽኑ መቋቋም ዐቢይ ዓላማ መሠረታዊ በሆኑ ሀገራዊ ጉዳዮች ረገድ የተፈጠሩ ልዩነቶችን በመለየት ውይይት ለማካሄድ መሆኑንም፤ ሰብሳቢዋ አብራርተዋል፡፡

በወቅቱ ከምክር ቤት አባላት ጥያቄና አስተያየት የተሰነዘረ ሲሆን ለአብነትም አዋጁ አሁን ሀገሪቱ ጦርነት ውስጥ ባለችበት፣ ሁሉም የህብረተሰብ ክፍሎች ሃሳባቸውን በበቂ ሁኔታ ለመግለጽ በማይችሉበት በዚህ አጭር ጊዜ ለውሳኔ መቅረቡ አግባብነት የሌለው መሆኑን የተከበሩ ዶ/ር ደሳለኝ ጫኔ አንስተዋል፡፡

ሌሎች የምክር ቤቱ አባላትም አክለው፤ አዋጁን ከምናጸድቅ ይልቅ አሁን በጦርነት የተጎዱ የህብረተሰብ ክፍሎችን ስነ-ልቦና ማከም እና ወደነበሩበት አካባቢ የመመለስ ሥራ ቅድሚያ ሊሰጠው እንደሚገባ አስተያየቸውን ሰጥተዋል፡፡

ይህ በእንዲህ እንዳለም ከተጠቀሰው ሐሳብ በተቃራኒ ወገን የቆሙ የምክር ቤት አባላት፤ ህብረተሰቡ አዋጁ ላይ ያለው አመለካከት ገና ያልጠራ ቢሆንም ግልጽነትን በመፍጠር ዋልታ-ረገጥ ሃሳቦችን ለማቀራረብ አዋጁ ጠቀሜታ እንዳለው አመላክተዋል፡፡

እነዚሁ የምክር ቤት አባላት አክለውም፤ ሀገሪቱን በሁሉም አቅጣጫ ከገጠማት ፈተና ለማላቀቅ እና ችግሮችን በተገቢው መንገድ ነቅሶ በማውጣት፣ በዘርፉ አበክሮ በመሥራት በሀገር በቀል ባህሎች እና እሴቶች አማካይነት ዘላቂ መፍትሔ ለማምጣት አዋጁ እንደሚያግዝ ጠቁመዋል፡፡

የቋሚ ኮሚቴው ሰብሳቢ የተከበሩ ወ/ሮ እጸገነት ከአባላት ለተነሳው ጥያቄ ምላሽ የሰጡ ሲሆን፤ አዋጁን ተንተርሰው በቀጣይ የሚወጡት መመሪያዎች እና ደንቦች ዝርዝር ምላሽ እንደሚኖራቸው፣ ከእርቀ-ሰላም ኮሚሽን እና መሰል ኮሚሽኖች ጋር ያለው ግንኙነትም በምክክር ሂደቱ ወቅት የሚታይ መሆኑን አስረድተዋል፡፡

በመጨረሻም ም/ቤቱ ሀገራዊ የምክክር ኮሚሽን ለማቋቋም የቀረበውን ረቂቅ አዋጅ በ13 ተቃውሞ፣ በአንድ ድምጸ-ተዓቅቦ በአብላጫ ድምፅ አጽድቋል፡፡

ሪፖርተር ኢያሱ ማቴዎስ