(ዜና ፓርላማ) ህዳር 10 ቀን 2014/ በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የህግ፣ ፍትህ እና ዴሞክራሲ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ በተያዘው በጀት ዓመት የህዝቡን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ የክትትል እና ቁጥጥር ስራው አጠናክሮ እንደሚቀጥል አስታውቋል፡፡

የቋሚ ኮሚቴው ሰብሳቢ የተከበሩ ወይዘሮ እፀገነት መንግስቱ እንደገለጹት፤ ኮሚቴው 2014 በጀት ዓመት እቅዱን ገምግሞ በማፅደቅ ስራውን በይፋ የጀመረ ሲሆን 24 ተቋማትን የሚከታተል ሲሆን፤ ከነዚህም መካከል የዲሞክራሲ እና የፍትህ ተቋማት እንደሚገኙበት ገልፀዋል፡፡

ቋሚ ኮሚቴው የሚከታተላቸውን ተቋማት እቅድ ከመገምገም ባለፈ በተግባር ወርዶ ያከናወኑትን ተግባር እንደሚያረጋግጥና ህዝቡ ሰብአዊና ዴሞካራሲያዊ መብቱ ተጠብቆ ተጠቃሚነቱን ለማረጋገጥ የህዝብ መድረክ እንደሚዘጋጅ የቋሚ የኮሚቴው ሰብሳቢ ተናግረዋል፡፡

የተከበሩ / እፀገነት እንዳሉት የተቋማት እቅድ የተግባር አፈጻጸም 10 አመቱ መሪ እቅድ ጋር የተቃኘ መሆኑን ጠቁመው፤ በቀጣይ በሚዘጋጀው የምዘና ማንዋል መሰረት ውጤታቸው የሚለካ እንደሆነ አመላክተዋል፡፡

ኮሚቴው 2014 በጀት ዓመት ለረቂቅ ህግ አዘገጃጀት፣ ለክትትልና ቁጥጥር ስራው ልዩ ትኩረት በመስጠት የህዝቡን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ ዘርፈ-ብዙ ስራዎች የሚከናወኑ መሆኑንም ሰብሳቢዋ ገልጸዋል፡፡

ቋሚ ኮሚቴው የሚከታተላቸውን ተቋማት እቅድ እና የተግባር አፈጻጸም በክትትልና ቁጥጥር ስራው ገምግሞ ክፍተቶችን ከማስተካከል ባለፈ በህግ ተጠያቂ የሚሆኑበት የአሰራር ስርዓት የተዘረጋ መሆኑን የቋሚ ኮሚቴው ሰብሳቢ የተከበሩ ወይዘሮ ፀገነት አስገንዝበዋል፡፡

ተስፋሁን ዋልተንጉስ