የኢፌዴሪ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ-ጉባዔ የተከበሩ ታገሠ ጫፎ እና የሶማሌ ክልል ርዕሰ-መስተዳድር ክቡር ሙስጠፌ መሐመድ፤ “ስለ ኢትዮጵያ” በሚል ርዕስ የተዘጋጀውን የፎቶ ዐውደ-ርዕይ መርቀው ከፈቱ፡፡

በዛሬው ዕለት በሶማሌ ክልል ርዕሰ-ከተማ በጅግጅጋ ለዕይታ የበቃውን ይህንን ዐውደ-ርዕይ የከፈቱት አፈ-ጉባዔ ታገሠ፤ ዐውደ-ርዕዩ እና ተከትሎት የተዘጋጀው የምክክር መድረክ፣ እንደ ሀገር የውይይት ባሕልን ለማዳበር እና ችግሮችን በውይይት መፍታትን ለመለማመድ እንደሚያግዝ ጠቁመዋል።

የፎቶግራፍ ዐውደ-ርዕዩ በአጼ ኃይለስላሴ፣ በደርግ፣ በኢሕአዴግ እንዲሁም በለውጡ መንግስት በነበሩ ዐበይት የታሪክ ክስተቶች ላይ ያጠነጠነ ሲሆን፤ ለሦስት ተከታታይ ቀናት ለሕዝብ ዕይታ ክፍት ሆኖ ይቆያል።

የፎቶግራፍ ዐውደ-ርዕዩ በክልል ደረጃ የመጀመሪያ ሲሆን፤ በሌሎችም ክልሎች የሚቀጥል መሆኑ ተገልጿል። ዐውደ-ርዕዩን ከፌዴራል እና ከክልል የመጡ እንግዶች እየጎበኙት ይገኛሉ።

ኢፕድ ከዚህ ቀደም "ስለኢትዮጵያ" እና "ዘመቻ ለፍትሕ" በተሰኙ ርዕሶች የፎቶግራፍ ዐውደ-ርዕይ ማዘጋጀቱ ይታወሳል።

በተመሳሳይ ዜናም፤ በአንጋፋው የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት የተዘጋጀው የፎቶ መጽሐፍ፤ በኢፌዴሪ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ-ጉባዔ በተከበሩ ታገሠ ጫፎ እና በሶማሌ ክልል ርዕሰ-መስተዳድር ክቡር ሙስጠፌ መሐመድ ተመርቋል፡፡

በመጽሐፉ ምረቃ ሥነ-ሥርዓት የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ጌትነት ታደሰ እንዳሉት፣ ወደፊትም እንዲህ ዓይነት መጽሐፍትን ያዘጋጃል። ድርጅቱ ከዚህ ቀደምም “አሻራ” የሚል መጽሐፍ አሳትሞ ለንባብ ማብቃቱ ይታወሳል።

በተያያዘ ዜናም፤ በኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት አዘጋጅነት “ኢትዮጵያ እያሸነፈች ትሻገራለች” በሚል መልዕክት የፓናል ውይይት በጅግጅጋ ከተማ እየተካሄደ ይገኛል።

“ኢትዮጵያ እያሸነፈች ትሻገራለች” በሚል ርዕስ በተዘጋጀው በዚሁ የፓናል ውይይት፤ የተለያዩ ጥናታዊ ጽሑፎች ቀርበው ውይይት እየተደረገባቸው ነው።

በፓናል ውይይቱም፤ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ-ጉባዔ ታገሠ ጫፎ፣ የሶማሌ ክልል ርዕሰ-መስተዳድር ሙስጠፌ መሐመድን ጨምሮ ሌሎች የፌዴራል እና የክልል መንግስታት ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች፣ የፖለቲካ ፓርቲ ተወካዮች፣ የኃይማኖት አባቶች፣ የሀገር ሽማግሌዎች እና የጅግጅጋ ከተማ ነዋሪዎች እየተሳተፉ እንደሚገኙ ከኢፕድ እና ከኢቢሲ ያገኘናቸው መረጃዎች ያመላክታሉ።