(ዜና ፓርላማ)፤ ጥር 2013 ዓ.ም.፣ ጊዳቦ፤ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የተፈጥሮ ሀብት፣ መስኖ እና ኢነርጂ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ቡድን ሰሞኑን በጊዳቦ መስኖ ልማት የመስክ ምልከታ ባደረገበት ወቅት፤ ፕሮጄክቱ ለአከባቢው ማኅበረሰብ እና ለተማሩ ወጣቶች የሥራ ዕድል ፈጠራ መዋል ሲገባው ዓላማውን ስቶ ለግል ባለሀብቶች ተላልፎ መሰጠት እንደሌለበት አሳሰበ፡፡

በኦሮሚያ እና በሲዳማ ክልሎች አዋሳኝ ቦታ ላይ የሚገኘው የጊዳቦ መስኖ ልማት ፕሮጀከት፤ 13ሺ ሄክታር መሬት ለማልማት ዕቅድ ተይዞለት በግንባታ ላይ የሚገኝ መሆኑን የቋሚ ኮሚቴ ቡድን ለመገንዘብ ችሏል፡፡ በኦሮሚያ ክልል በኩል የፕሮጄክቱ ዋና ቦይ ተፋሰስ ሥራ 96 በመቶ የተጠናቀቀ ሲሆን፤ በአንጻሩ በሲዳማ ክልላዊ መንግስት በኩል ግን የፕሮጄክቱ ግንባታ 34 በመቶ ላይ እንደሚገኝም አረጋግጧል፡፡

ለተማሩ የኦሮሚያ ወጣቶች የሥራ ዕድል ከመፍጠር አኳያ፤ በዘርፉ ስልጠና ተሰጥቶ ለመስኖ የሚሆን መሬት የተዘጋጀ መሆኑን እና ለአከባቢው ማኅበረሰብም የተሟላ መሠረተ-ልማት መዘርጋቱን አባላቱ በመስክ ጉብኝታቸው ተመልክተዋል፡፡ የኦሮሚያ ክልላዊ መንግስት በመስኖ ልማት ፕሮጄክቱ 8ሺ ሄክታር ለማልማት ዕቅድ ይዞ ወደ ተግባር በመግባት፤ በ350 ሄክታር መሬት ላይ በአካባቢው አርሶ-አደር የመስኖ ልማት ጀምሯል፡፡

በሲዳማ ክልላዊ መንግስት በኩል በመስኖ ፕሮጄክቱ 5ሺ ሄክታር ለማልማት ታቅዶ እንደነበር መረጃዎች ያሳያሉ፡፡ ዳሩ ግን የአከባቢውን አርሶ-አደር ከማሳተፍም ሆነ የተማሩ ወጣቶችን መልምሎ ስልጠና ከመስጠት አንጻር የአከናወነው ተግባር እንደሌለ እና በፕሮጄክቱ ግንባታ ሂደትም የሚያደርገው ትብብር እና ድጋፍ ዝቅተኛ መሆኑን የኮሚቴው ቡድን ተረድቷል፡፡

ቡድኑ በመስኖ ፕሮጄክቱ የአደረገውን የመስክ ምልከታ ከአጠናቀቀ በኋላ የሲዳማ ክልላዊ መንግስት አመራሮችን ሰብስቦ አወያይቷል፡፡ የፕሬዚዳንቱ አማካሪ አቶ ተሰማ ዲማ በዚህን ወቅት እንደገለጹት፤ በአለፉት ወራት በክልል አደረጃጀት ምክኒያት ለመስኖ ፕሮጄክቱ ትኩረት አልተሰጠውም፡፡ በቀጣይ ግን ክልሉ ለፕሮጄክቱ ተቋራጮች አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርግ ቃል ገብተዋል፡፡

የሎካ አባያ ወረዳ አስተዳደር አቶ ዘገየ ኮይሳ በበኩላቸው፤ የፕሮጄክቱ ግንባታ ሲጀመር ኢ-ፍትሐዊ እና አድሎአዊ አሠራር እንደነበረበት ገልጸዋል፡፡ ለአብነትም፤ በሲዳማ ክልል በኩል የፕሮጄክቱ ግንባታ እንዲጓተት እና ለማኅበረሰቡም የመሠረተ-ልማት ግንባታ የመዘርጋቱ  ነገር ታሳቢ እንዳልተደረገ አስታውሰዋል፡፡

በኢትዮጵያ ኮንስትራክሽን ሥራዎች ኮርፖሬሽን የውኃ እና መሠረተ-ልማት ሥራ አስኪያጅ አቶ አለማየሁ በቀለ በበኩላቸው፤ በመስኖ ልማት ፕሮጄክቱ ግንባታ ሂደት አድሎአዊ አሠራር የለም ብለዋል፡፡ በኦሮሚያ ክልል በኩል አመራሮች በግንባታው ሂደት የሚያደርጉት ድጋፍ እና ክትትል የተጠናከረ ሲሆን፤ በተቃራኒው ከሲዳማ ክልል አመራሮች የሚደረገው ድጋፍ እና ትብብር ውስንነት እንደነበረው አስረድተዋል፡፡ ይሁን እንጂ አጠቃላይ የመስኖ ፕሮጄክቱን ግንባታ እስከ ሰኔ 30 ቀን 2013 ዓ.ም. ለማጠናቀቅ ጥረት እየተደረገ መሆኑን አያይዘው አስታውቀዋል፡፡

የተፈጥሮ ሀብት፣ መስኖ እና ኢነርጂ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ አባል እና የቡድኑ አስተባባሪ የተከበሩ አቶ ሰጠኝ አዲሱ በግብረ-መልሳቸው፤ ለብዙ ዓመታት የተጓተተውን የመስኖ ፕሮጄክት ግንባታ በተያዘው በጀት ዓመት ለማጠናቀቅ ዕቅድ መያዙ፣ ግንባታው በሀገር-በቀል መኅንዲሶች በጥራት እየተገነባ መሆኑ እና የግንባታ ሥራው እንዳይደናቀፍ በፀጥታው ዘርፍ ትኩረት መደረጉን በጥንካሬ አንስተዋል፡፡

በአንጻሩ፤ በሲዳማ ክልል በኩል የአከባቢውን አርሶ-አደር እና የተማሩ ወጣቶችን በመስኖ ፕሮጄክቱ ተጠቃሚ ከማድረግ አንጻር ትኩረት አለመሰጠቱ፣ በግንባታ ሂደቱ የክልሉ መንግስት ተሳትፎ ዝቅተኛ መሆኑ እንዲሁም ለወጣቶች የሥራ ዕድል ፈጠራ ይሆናል የተባለው የመስኖ መሬት ለግል ባለሀብቶች ተላልፎ መሰጠቱ በርሳቸው በክፍተት የተመላከቱ ጉዳዮች ናቸው፡፡

በተያያዘ ዜናም፤ ቋሚ ኮሚቴው ንጹህ የመጠጥ ውኃን አስመልክቶ በዲላ ከተማ የመስክ ምልከታ በአደረገበት ወቅት፤ በከተማዋ ከፍተኛ የውኃ ችግር መኖሩን አረጋግጧል፡፡ የከተማዋ የውኃ መስመሮች የአረጁ እና የተበላሹ በመሆናቸው 40 በመቶ የውኃ ብክነት እንዳለ ተገንዝቧል፡፡

ከከተማዋ መልክዓ-ምድር አኳያ ከፍተኛ ቦታ ላይ ለሚገኙ ሰፈሮች ውኃ የማይደርስ ሲሆን፤ ውኃ ተደራሽ ነው በሚባልባቸው የከተማዋ ክፍሎች ደግሞ ከ15 ቀን በላይ እንደሚጠፋ ከከተማው ነዋሪዎች መረዳት ተችሏል፡፡

በዲላ ከተማ አስተዳደር የውኃ አገልግሎት ሥራ አስኪያጅ አቶ ፍስሐ ኡዶ፤ የከተማዋን የውኃ ችግር በዘላቂነት ለመቅረፍ ታስቦ በውኃ ፈንድ ድጋፍ የሚገነባው ፕሮጄክት ለ10 ዓመታት መጓተቱን በምሬት ያስታውሳሉ፡፡ ግንባታው ተፋጥኖ የአራት ጥልቅ ጉድጓዶች ሥራ ቢጠናቀቅም፤ ከከተማው ሕዝብ ብዛት አንጻር ችግሩን ሊፈታ እንዳልቻለ ተናግረዋል፡፡

በባለሙያዎች በተደረገው ጥናትም የከተማዋ የውኃ ሽፋን 16 በመቶ ብቻ መሆኑን አቶ ፍስሐ ለቋሚ ኮሚቴው ቡድን አክለው አስገንዝበዋል፡፡

ቡድኑ በበኩሉ፤ የዲላ ከተማ የውኃ ችግር በዘላቂነት እንዲፈታ በየደረጃው የአሉ አመራሮች እና የከተማ አስተዳደሩ በቅንጅት መሥራት እንዳለባቸው አሳስቧል፡፡

ዘጋቢ ተስፋሁን ዋልተንጉስ