(ዜና ፓርላማ)፤ ግንቦት 16፣ 2014 ዓ.ም.፤ አዲስ አበባ፤ የማዕድን ዘርፉ፤ የኢትዮጵያን የብልጽግና ጉዞ ለማሳካት ተስፋ እንደተጣለበት፣ በኢፌዴሪ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ተገለጸ፡፡

ፓርላማው ይህንን የገለጸው፤ የማዕድን ሚኒስቴርን የዘጠኝ ወራት የዕቅድ አፈጻጸም ሪፖርት ባዳመጠበት በዛሬው ዕለት በሰጠው አስተያየት ነው፡፡ ይህ የ6ኛው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት 1ኛ ዓመት የሥራ ዘመን 9ኛ መደበኛ ጉባዔ፤ በሚኒስቴሩ የማዕድን ዘርፍ የተከናወኑ ተግባራትን በዝርዝር ተመልክቷል፡፡

ሀገሪቱ ከነበሩባት ውስብስብ ችግሮች የተነሳ ከማዕድን ሀብት ተጠቃሚ እንዳልነበረች የሚታወቅ ቢሆንም፤ ከለውጡ ወዲህ ግን በማዕድን ዘርፉ የተመዘገቡ ውጤቶች የኢትዮጵያን ብልጽግና የማሳካት ተስፋ አሰንቀዋል፡፡ ዘርፉ በራሱ ከብዝኃ-ኢኮኖሚ ምሰሶዎች አንዱ መሆኑን ምክር ቤቱ ተገንዝቧል፡፡

በማዕድን ዘርፉ ኢትየጵያን ተጠቃሚ ለማድረግ ተጨባጭ ለውጥ መምጣት እንዳለበት እና ከውጭ የሚገቡትን የማዕድናት ውጤቶች በአገር ውስጥ ምርቶች ለመተካት የሚደረገው ጥረት የበለጠ መጠናከር እንዳለበት ምክር ቤቱ አሳስቧል፡፡

ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ ባለፉት ዘጠኝ ወራት ውስጥ የወጪ ንግድን ለማሳደግ፣ የገቢ ምርቶችን በሀገር ውስጥ ምርቶች ለመተካት እና የዜጎችን የሥራ ዕድል ፈጠራ የበለጠ ለማስፋት ትኩረት ሰጥቶ እየሠራ እንደሆነ እና የረጅም ጊዜ ዕቅዱን ከግብ ለማድረስ ፖሊሲ፣ ደንብ እና መመሪያዎችን ለማሻሻል ጥረት ማድረጉንም ምክር ቤቱ መረዳት ችሏል፡፡

በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የማዕድን እና ኢንዱስትሪ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ የተከበሩ አማረች በካሎ (ዶ/ር)፤ ማዕድን ሚኒስቴር የሀገሪቱ ኢኮኖሚ የጀርባ አጥንት እንደሆነ በመንግስት ታምኖበት የተቋቋመ ሲሆን፣ ከዚህ ተቋም ሕዝብ እና መንግስት የላቀ ውጤት እንደሚጠብቁ አስታውቀዋል፡፡

በማዕድን ዘርፉ ዕውቀት ያለው ዜጋ ለማፍራት በከፍተኛ የትምህርት ተቋማት የማዕድን ማዕከላት መከፈታቸውን ሰብሳቢዋ ይበል ብለዋል። በሌላ በኩልም የሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ ተጠሪ ተቋማት ወደ አንድ ማዕከል እንዲሰባሰቡ መደረጉ የበጀት ወጪን ለመቀነስ እና ለሥራዎች ቅልጥፍና ጥሩ ተሞክሮ መሆኑን ዶክተር አማረች በአድናቆት ተመልክተዋል፡፡

ሀገሪቱ ያላት ዕምቅ የማዕድን ሀብት ለሕዝብ ዕይታ እንዲውል የማዕድን ጋለሪ መዘጋጀቱ እና ማዕድን በሚወጣባቸው አካባቢዎች የጸጥታ ችግር እንዳይከሰት በቅንጅት መሠራቱ በጥሩ ጎን የሚታዩ ተግባራት መሆናቸውን ሰብሳቢዋ አክለው አስረድተዋል፡፡ የማዕድን ዘርፍ በተፈጥሮው ከውጭም ከውስጥም ከፍተኛ ፍላጎት እና ዐይን የሚያርፍበት በመሆኑ፤ ተቋሙ ሕገ-ወጥነትን ለመከላከል ከተጠሪ ተቋማት እና ከፍትሕ አካላት ጋር በቅንጅት በመሥራት ቀጣይነት ያለው ዕድገት እንዲመዘገብ ጥረት መደረግ እንዳለበትም የተከበሩ ዶክተር አማረች አስገንዝበዋል፡፡

ማዕድናት በሚመረቱበት አካባቢ የአድሎዊነት፣ የአለመረጋጋት እና የግጭት መንስዔ እንዳይሆኑ ተቋሙ ኃላፊነት መውሰድ እንዳለበት የጠቆሙት ሰብሳቢዋ፤ የተቋሙ የማዕድን ጥናቶች በዳታ ቤዝ መያዝ እንዳለባቸው እና ዓለም-አቀፋዊ ተወዳዳሪ ሊሆኑ እንዲሚገባም አመላክተዋል፡፡

ወርቅን ጨምሮ የማዕድን ሽያጮች ዓለም-አቀፍ የግብይት ስታንዳርዶችን ያሟሉ መሆን እንዳለበት እና የምርቶቹ ጥራት ተጠብቆ ከብክነት የጸዳ የአሠራር ሥርዓት ሊኖር እንደሚገባ የተከበሩ ዶክተር አማረች አሳስበዋል፡፡

የምክር ቤት አባላት በበኩላቸው፤ ሀገሪቱ ከማዕድን ዘርፍ የሚጠበቀውን ጥቅም ማግኘት እንዳለባት አመላክተው፤ በማዳበሪያ፣ በድንጋይ ከሰል እና ብረት ምርት ላይ ተቋሙ በትኩረት ሊሠራ እንደሚገባ እና ተጨባጭ ውጤት መታየት እንዳለበት ጠቁመዋል፡፡

የማዕድን ሚኒስትር ክቡር አቶ ታከለ ኡማ በበኩላቸው፤ ማዳበሪያ በሀገር ውስጥ አምርቶ አርሶ -አደሩን ተጠቃሚ ለማድረግ የኢትዮጵያ የብልጽግና መንግስት የሞት የሽረት ጉዳይ እንደሆነ አስረድተዋል። ማዳበሪያ ለማምረት የሚያስፈልጉ ግብዓቶች በሀገር ውስጥ የሚገኙ መሆናቸውንም አስታውሰዋል፡፡

የድንጋይ ከሰል ከቀጣይ ጥቂት ወራቶች በኋላ በሀገር ውስጥ ለማምረት ቅድመ-ዝግጅቱ መጠናቀቁን የገለጹት ክቡር ሚኒስትሩ፤ በነዳጅ እና ተፈጥሮ ጋዝ እንዲሁም በወርቅ ምርት እና ፍለጋ ተሰማርተው በዕቅዳቸው መሠረት መጓዝ ባልቻሉ ኩባኒያዎች ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ ርምጃ እየወሰደ እንደሆነም ገልጸዋል፡፡

ተቋሙ ባለፉት ዘመናት ተኩረት ተነፍጎት የቆየ በመሆኑ ከወደቀበት ለማንሳት ሁለንተናዊ ጥረት እየተደረገ እንደሆነ እና ከማዕድን ዘርፍ የሚፈለገውን ጥቅም በዘላቂነት ለማግኘት የፖሊሲ፣ ደንብ እና መመሪያ ማሻሻያዎችን እየሠራን ነው ሲሉ ሚኒስትሩ አብራርተዋል፡፡

በዘንድሮ በጀት ዓመት በአለፉት ዘጠኝ ወራት ለውጭ ገበያ ከቀረቡ የወርቅ፣ የጌጣ-ጌጥ እና የኢንዱስትሪ ማዕድናት በድምሩ 458 ነጥብ 07 ሚሊየን ዶላር የውጭ ምንዛሬ መገኘቱን አቶ ታከለ ይፋ አድርገዋል፡፡

ሚኒስትሩ አያይዘውም፤ በሲሚንቶ ምርት ስወራ እና የዋጋ ንረት የተሳተፉ ደላሎች ከገበያ እንዲወጡ የአሠራር ሥርዓት ተዘርግቶ ርምጃ እየተወሰደ እንደሆነም ገልጸዋል፡፡

በ ተስፋሁን ዋልተንጉስ