null “Ethiopia values longstanding people-to-people ties with Sudan”

ኢትዮጵያ የሱዳንን የሕዝብ ለሕዝብ ዲፕሎማሲ ልዑካን ተቀበለች

ኀዳር 12፣ 2012 ዓ.ም. አዲስ አበባ፤ ከጎረቤት ሀገር ሱዳን የመጣውን የሕዝብ ለሕዝብ ዲፕሎማሲ ልዑካን ኢትዮጵያ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አማካይነት ተቀበለች፡፡

በሁለቱ ሀገራት ሁለንተናዊ የጋራ ጉዳዮች የሚመክረው ይኸው የሕዝብ ለሕዝብ የዲፕሎማሲ ልዑካን ሰሞኑን በተደረገለት አቀባበል፤ የኢፌዴሪ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ-ጉባዔ ክቡር ታገሰ ጫፎ የእንኳን ደህና መጣችሁ ንግግር አሰምተዋል፡፡ በንግግራቸውም፤ ኢትዮጵያ ከሱዳን ጋር የመሠረተቸውን የረዥም ጊዜ የሕዝብ ለሕዝብ ግኝኙነት በአክብሮት እንደምታይ ገልጸዋል፡፡

ለቱ ሀገራት በመልክዓ-ምድር የተሳሰሩ ብቻ ሳይሆኑ፣ ሊለያዩ በማይችሉበት ደረጃ በተፈጥሮ እና በታሪካዊ ሁኔታዎች የተሳሰሩ መሆናቸውን ያመላከቱት አፈ-ጉባዔው፤ የታሪክ፣ የቋንቋ፣ የአኗኗር ዘይቤ እና ሌሎች የጋራ ማኀበራዊ ጉዳዮችም እንደሚያስተሳስሯቸው አስረድተዋል፡፡ ለዚህም የአክሱምን እና የመሮዌን ስልጣኔ እንዲሁም የናይል ወንዝ የጋራ ፀጋን በአብነት አንስተዋል፡፡

ክቡር አፈ-ጉባዔው፤ ሁለቱ ሀገራት በፖለቲካ፣ በምጣኔ-ሀብት፣ በማኀበራዊ እና መሰል ጉዳዮች ያላቸውን ትስስር ለማስቀጠል የሚረዱ አሠራሮችን መዘርጋታቸውንም በአድናቆት አስታውሰዋል፡፡ አያይዘውም፤ የሁለቱ እህትማማች ሀገራት ትብብር በመሠረተ-ልማቱም ጭምር እየጎለበተ መምጣቱን ጠቁመዋል፡፡

ሱዳን በቅርቡ ያካሄደችውን የስልጣን ሽግግር ኢትዮጵያ እንደምታደንቅ የገለጹት አቶ ታገሰ ጫፎ፤ ሀገሪቱ የመላው ሱዳናዊያንን ተጠቃሚነት በአረጋገጠ መልኩ የፈጸመችውን ስምምነት ለመተግበር መዘጋጀቷ ይበል የሚያሰኝ ነው ብለዋል፡፡

ከታላቁ የኢትዮጵያ የሕዳሴ ግድብ ግንባታ ጋር በተገናኘም ሱዳን በመርህ ላይ የተመሠረተ አካሄድ መከተሏን አፈ-ጉባዔው አስታውሰው፤ ኢትዮጵያ ያላት የፀና የጋራ ተጠቃሚነት መርህ እንደማይለወጥም አስገንዝበዋል፡፡

የመጀመሪያው የሱዳን የሕዝብ ለሕዝብ የዲፕሎማሲ ልዑካን በ2007 ዓ.ም. ተመሳሳይ ጉብኝት ያካሄደ ሲሆን፤ መረጃዎች እንደሚያሳዩት የአሁኑ ለሁለተኛ ጊዜ ነው፡፡ የኢትዮጵያው አቻ ቡድንም በ2008 ዓ.ም. ተመሳሳይ የሥራ ጉብኝት በጎረቤት ሱዳን ማካሄዱ ይታወሳል፡፡

 

አሥራት አዲሱ

  የምክር ቤት ዘጋቢ