null A delegation led by Slovenian president visits the parliament.

ስሎቫኒያ ከኢትዮጵያ ጋር የዲፕሎማሲ ግንኙነት መፍጠሯ ከሌሎች የአፍሪካ አገራት ጋር በቀላሉ ለመገናኘት የተሻለ እድል እንደሚፈጥር ተገለጸ፡፡

ጥቅምት 07 ቀን 2011 ዓ.ም.- የስሎቫኒያ ሪፐብሊክ ልኡካን ቡድን በኢትዮጵያ ይፋዊ የስራ ጎብኝት ሲካሂድ መቆየቱ የሚታወቅ ሲሆን በዛሬው እለት በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የመጨረሻውን ጉብኝት አጠናቋል፡፡

የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ምክትል አፈ-ጉባኤ ወ/ሮ ሽታዬ ምናለ ልዑካን ቡድኑን ተቀብለው ባነጋገሩበት ወቅት በሁለቱ አገሮች መካከል የህዝብ ለህዝብ እና የፓርላማ ግንኙነት እንዲጠናከር ዘርፈ-ብዙ ስራዎች መሰራት እንዳለበት ገልፀዋል፡፡

በህዳሴው ግድብ ዙሪያ ኢትዮጵያ ከሱዳንና ከግብፅ ጋር የሶስትዮሽ ስምምነት ተፈራርማ ከ6 ሺህ ሜጋዋት በላይ የሚያመነጭ ትልቅ የሀይድሮ ኤሌክትሪክ ፓወር እየገነባች የምትገኝ ሲሆን፣ ግድቡ በታችኛው ተፋሰስ አገራት ላይ ምንም አይነት አሉታዊ ተፅዕኖ እንደማያሳድር በእውቅ ባለሙያዎች የተረጋገጠ መሆኑን ምክትል አፈ-ጉባኤ ወ/ሮ ሽታዬ ተናግረዋል፡፡

ኢትዮጵያ በምስራቅ አፍሪካ ሰላምን በዘላቂነት ለማስፈን የምታደርገውን ሁለንታናዊ እንቅስቃሴን ለልኡካኑ የገለጹ ሲሆን በሶማሊያ እና በደቡብ ሱዳን ያደረገቻቸው የሰላም ድርድሮች ውጤታማና ተስፋ ሰጭ መሆናቸውንም አስረድተዋል፡፡

የውጭ ጉዳይ ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ የተከበሩ አቶ ተስፋዬ ዳባ ስሎቫኒያ በኢንቨስትመንት፣ በቱሪዝም፣ በአግሮ ኢንዱስትሪና በንብ ማነብ ዘርፎች ጥልቅ እውቀት ያላት በመሆኗ ኢትዮጵያም ይህን ጠቃሚ እውቀት የልምድ ተሞክሮ ለመቅሰምና የወዳጅነት ስምምነቱን አጠናክራ ለመቀጠል ፍላጎት ያላት መሆኑን ተናግረዋል፡፡

አክለውም ስሎቫኒያ በምስራቅ ውሮፓ የምትገኝ አገር ስትሆን ልኡካኑ በኢትዮጵያ ለመጀመሪያ ጊዜ  ይፋዊ የስራ ጉብኝት ማድረጉ ታሪካዊ ከመሆኑም ባሻገር የሁለቱን አገሮች ግንኙነት አጠናክሮ ለማስቀጠል የስምምነት ፊርማ መፈጸሙን ገልጸዋል፡፡      

የልኡካን ቡድኑ አባላት በበኩላቸው ኢትዮጵያ እምቅ የተፈጥሮ ሀብት ባለጸጋ ከመሆኗም ባለፈ ህዝቦቿ ስራ ወዳድ እና እንግዳ ተቀባይ መሆናቸው ማረጋገጥ ችለናል ሲሉ ተናግረዋል፡፡

በሌላ በኩልም ስሎቫኒያ ከኢትዮጵያ ጋር የድፕሎማሲ ግንኙነት ፈጠረች ማለት ከሌሎች የአፍሪካ አገራት ጋር በቀላሉ ለመገናኘት እንደ ድልድይ ሆኖ የሚጠቅም በመሆኑ ለተለያዩ የኢንቨስትመንት አማራጭ እድሎችን ሊከፍት እንደሚችል ተስፋ እናደርጋለን ብለዋል፡፡

በመጨረሻም የልኡካን ቡድኑ የፓርላማውን መሰብሰቢያ አዳራሽና ሕንፃ ተዘዋውረው ገብኝተዋል፡፡