null Committee of the House said that the water supply at Mekele city is not appropriate to its ever increasing population.

የመቐለ ከተማ የመጠጥ ውሀ አቅርቦት እያደገ ከመጣው የህዝብ ቁጥር ጋር ባለመመጣጠኑ ነዋሪዎች ለችግር መጋለጣቸውን በኢፌዴሪ የህዝብ ተወዮች ም/ቤት ለተፈጥሮ ሀብት፣ መስኖና ኢነርጂ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ገለጹ፡፡

መጋቢት 23 ቀን 2011 ዓ.ም ይህ የተገለጸው ቋሚ ኮሚቴው በከተማና በዙሪያዋ ባደረገው መስክ ምልከታ ወቅት ነው፡፡

ቋሚ ኮሚቴ በፌደራል መንግስት በጀት የተገነቡትን የአይናለምና የጭን ፈረስ የመጠጥ ውሀ አቅርቦት ፕሮጀክቶችን የስራ እንቅስቃሴ ተዟዙሮ ጎብኝቷል፡፡

በጉብኝቱም ቋሚ ኮሚቴ የፕሮጀክቶቹን የስራ ሃላፊዎች፣ የውሀ ኮሚቴ ተወካዮች፣ የግል ባለሀብቶችንና ነዋሪዎችን አወያይቷ፡፡

የመቐለ ከተማ የውሃ አቅርቦትና የመጠጥ ውሀ አገልግሎት ም/ኃላፊ የሆኑት አቶ ብርሀኑ ገ/ኪሮስ በሁለቱ ፕሮጀክቶች ከተቆፈሩት የውሀ ጉድጓዶች ውስጥ 4ቱ ሙሉ በሙሉ መድረቃቸውንና የከርሰ ምድር ውሀ እየራቀ በመምጣቱ ቀሪዎቹ ጉድጓዶች የሚሰጡትን የውሀ መጠን በከፍተኛ ሁኔታ እየቀነሱ መምጣታቸውን ገልፀዋል፡፡

የሚገኘውም ውሃ የጥራት ችግር ያለበት ከመሆኑም ባሻገር ቁጥሩ እየጨመረ ለመጣው ነዋሪ በአግባቡ ለማዳረስ እንዳለተቻለ ተናግረዋል፡፡ አስፈላጊው የማጣራት ስራ ቢሰራም ውሀው ውስጥ ከፍተኛ ማዕድናት የሚገኙና በቆይታም እየዘቀጡ የሚመጡ በመሆኑ ቱቦዎችን በመዝጋትና በማጣሪው ላይም ብልሽት በመፍጠር ችግሩን እያባባሰው እንደመጣም አስረድተዋል፡፡

አክለውም በከተማ አስተዳደሩ በኩል በቦቴዎች በማዞር ለነዋሪዎች ንፁህ የመጠጥ ውሀ ለማዳረስ ጥረት ቢደረግም ችግሩን ሙሉ በሙሉ ለመፍታት ባለመቻሉ በመንግስት በኩል ዘላቂ መፍትሄ ሊበጅለት እንደሚገባ ነው ሃላፊው የጠቆሙት፡፡

የከተማውዋ ነዋሪዎችና የውሀ ኮሚቴ ተወካዮች በበኩላቸው የመጠጥ ውሃ የሚያገኙት በፈረቃ በሳምንት ሁለት ጊዜ እሱም ከፍተኛ የጥራት መጓደል የሚታይበትና በቱቦ መዘጋት ምክያንት ቱቦው እስኪጠረግ ተራቸው እንደሚያልፍ እንዲሁም ንፅህናው ያልተጠበቀ የጉድጓድ ውሀ እንዲጠቀሙ በመገደዳቸው ልጆቻቸው ለአተትና ለሌሎች ተዛማች በሽታዎች እየተጋለጡ መሆኑን በውይይት መድረኩ በምሬት ገልፀዋል፡፡

በሌላ በኩልም የግል ባለሀብቶች የተለያዩ ኢንዱስትሪዎችን በመክፈትና የስራ እድል በመፍጠር አገራቸውንና ራሳቸውን ለመጥቀም ቢነሱም በቂ የውሀ አቅርቦት ባለመኖኑ ለጉዳት መዳረጋቸውንና አንዳንድ ድርጀቶችም በዚህ ምክንት በደረሰባቸው ኪሳራ ለሀራጅ መቅረባቸውንም ለቋሚ ኮሚቴ ተናግረዋል፡፡

ባለሀብቱ መንግስትን ለማገዝ ለውሀ አገልጎሎት በገንዘብ የራሱን አስተዋጽኦ ቢያደርግም የታየ ለውጥ ባለመኖሩ በመንግስት ግባ ላይ ይገነባል የተባለውን ግድብ በመገደብ ችግራቸው በዘላቂነት እንዲፈታ፣ ቡድኑም ጉዳዩን በጥሞና እንዲያየውና ለሚመለከተው አካል በማቅረብም የበኩሉን ሚና እንዲወጣም ጠይቀዋል፡፡

የቋሚ ኮሚቴ አባላትም ችግሩ ከባሰባቸው አካባቢዎች አንዷ በሆነችው ሞሞና ቀበሌ በአካል በመኘትም ነዋሪዎችን አነጋግረዋል፤ ለነዋሪዎች በቦቴ በማዞር የሚደረገውን የመጠጥ ውሀ እደላምንም ታዝበዋል፡፡

የስራ ሃላፊዎችም በነዋሪዎች የቀረበው ቅሬታ ትክክለኛ መሆኑን ጠቁመው በቀጣይ ችግሩን ለመቅረፍ በርትተው እንደሚሰሩ ጠቁመዋል፡፡

በመጨረሻም የንዕስ ቋሚ ኮሚቴው ሰብሳቢና የቡድኑ መሪ የተከበሩ አቶ ዓለሙ ዲንቃ በሰጡት ማጠቃለያ በተደረገው የመስክ ምልከታ ቡድኑ የችግሩን ስፋት ለመታዘብ መቻሉን ጠቁመው፤ ባለሀብቱና ነዋሪዎች ችግሩን በትዕግስት ለማለፍ መቻላቸውንና በገንዘብና በጉልበት መንግስትን ለመደገፍ ጥረት ማድረጋቸውን አድንቀዋል፡፡

በቀጣም ችግሩ በዘላቂነት ምላሽ እንዲገኝ ቡድኑ ጥያቄውን ለሚመለከተው አካል በማቅረብ ድርሻውን እንደሚወጣም ነው ሰብሳቢው የተናገሩት፡፡