null Committee of the House urged Gambella University to solve its problems of good governance immediately.

ጋምቤላ ዩኒቨርስቲ   ያሉበትን  የመልካም አስተዳደር ችግሮች ፈጥኖ እንዲፈታ በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የሰው ሀብትና ቴክኖሎጅ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ አሳሰበ፡፡

ቋሚ ኮሚቴው  በዩኒቨርስቲው  በመገኘት የመስክ ምልከታ  ያካሄደ ሲሆን፤ የመልካም አስተዳደር ችግሮች እና  በርካታ የኪራይ ሰብሳቢነት ተግባራት እንደሚስተዋሉ ነው   መገንዘብ የቻለው፡፡

የጋምቤላ ዩኒቨርስቲ  ወደ ዩኒቨርስቲ  ከማደጉ በፊት የቴክኒክና ሙያ  ማሰልጠኛ የነበረ ሲሆን፤ በ2007 ዓ.ም ከመቱ   1500 ተማሪዎችን ተቀብሎ     በጀት ሳይኖረን ስራ መጀመሩን ዩኒቨርስትው ፕሬዚዳንት  ዶ/ር ኡጁሉ ኡኮክ  ገልፀው በአሁን ወቅት ዩኒቨርስቲው   ዘርፈ ብዙ  ችግሮች   እንዳሉበት  ለቋሚ ኮሚቴው አስገንዝበዋል፡፡

የዋናው ግቢ ህንፃ ግንባታ በበጀት ተደግፎ ባለመጀመሩ ምክንያት በግንቦት 25/2008 ዓም ተጀምሮ በሰኔ 15/2009 ዓ.ም ይጠናቀቃል ተብሎ ቢታቀደም በተያዘለት ጊዜ  ውስጥ ግን ማጠናቀቅ አልተቻለም፤  የግንባታው ሂደት በአሁን ወቅት  70 በመቶ  የደረሰ ሲሆን፤  በዚህ ሁኔታ ከቀጠለ በቀጣይ ዓመትም  ቢሆን ግንባታው ተጠናቆ  ስራ ለመጀመር አዳጋች ይሆናል ነው የተባለው፡፡  

ቋሚ ኮሚቴው  ከዩኒቨርስቲው  ማህብረሰብ ጋር ባደረገው ውይይት የትምህርት ጥራትን ከማስጠበቅ አኳያ በተማሪዎችና መምህራን  መካከል የዳበረ ዴሞክራሲያዊ ግንኙነት አለመዳበሩ፤  የቅሬታና የአቤቱታ  አፈታት ስርዓት በአግባቡ አለመዘርጋቱ፣ የተማሪዎች ዉጤትን  በወቅቱ አለማሳወቅ እንደችግር ከተነሱት መካከል ናቸው ፡፡

ለሴቶችና ለአካል ጉዳተኞች ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራ እንዳልሆነና ባለፉት ዓመታት  ልዩ ድጋፍ ለሚያስፈልጋቸው ተማሪዎችና አካል ጉዳተኞች ይሰጥ የነበረው የቱቶሪያል ትምህርት  በዚህ ዓመት  መቋረጡ ታውቋል፡፡

በተጨማሪም ምቹ የመማር ማስተማር አካባቢን ከመፍጠር አኳያም ውስንነት እንዳለ ነው ቋሚ ኮሚቴው የተገነዘበው፡፡  በዚህም ሳቢያ የፀጥታ ችግር መኖሩና በተለይ  ሴት ተማሪዎች ጥቃት እየደረሰባቸው ሲሆን በቅርቡም በአንድ  የአካል ጉዳተኛ ሴት ተማሪ  ላይ በማይታወቁ ግለሰቦች ጥቃት ተፈፅሟል፡፡በግቢው ውስጥ የመብራት፣ውሃና የመንገድ  ችግር እንዳለም   ታውቋል፡፡

የማበረታቻ ስርዓት ተዘርግቶ በመጠኑ  ተግባራዊ እተደረገ ቢሆንም  የሚሰጠው ማበረታቻና ጥቅማ ጥቅም  በትውውቅና በቅርርቦሽ እንደሆነ ሰራተኞች በመድረኩ ላይ ያነሱት አስተያየት አመላካች እንደሆነ  ቋሚ ኮሚቴው  ገምግሟል፡፡

ተማሪዎች የ2010 ዓ.ም የሁለተኛዉ ወሰነ ትምህርት ዉጤት እስካሁን አለማወቃቸዉ በመምህራን በኩል ክፍተት እንዳለ እና  የሬጅስትራ ሰራተኞች ላይም  የእውቀት  ውስንነት እና ቸልተኝነት በስፋት የሚስተዋል መሆኑን   ቋሚ ኮሜቴው በሰጠው ግብረ መልስ አመላክቷል፡፡

ዩኒቨርሲቲዉ ከአካባቢዉ ማህበረሰብ ጋር ያለዉ ቁርኝት እጅግ በጣም አነስተኛ በመሆኑ ተማሪዎች የአካባቢዉን ማህበረሰብ እንደስጋት የሚያዩት ሲሆን፤የዩንቨርስቲው አመራር ከሚመለከተው አካል ጋር በመሆን ችግሩን  ሊቀርፍ ይገባል ሲል  ቋሚ ኮሜቴው አሳስቧል፡፡