null Committee of the House urged all Universities should have balanced capacity

በሃገሪቱ ውስጥ ያሉ ሁሉም ዩኒቨርሲቲዎች  የተመጣጠነ አቅም እንዲኖራቸው ሊሠራ እንደሚገባ በህዝብ ተወካዮች ም/ቤት የሠው ሃብትና ቴክኖሎጂ ጉዳዩች ቋሚ ኮሚቴ ሠብሳቢ ወ/ሮ እምዬ ቢተው አሣሠቡ፡፡

የቋሚ ኮሚቴው አባላት ሰሞኑን በጅማና በጋምቤላ ዩኒቨርስቲዎች የመስክ ምልከታ አድርገዋል፡፡

በመስክ ምልከታው ወቅት የታዩ ጠንካራ ጐኖችን የበለጠ እንዲጐለብቱና ድክመት የታየባቸውን አፈፃፀሞች በመለየት እንዲታረሙ ለሚመለከተው አካል ትላንት ራፖርት ቀርቦ ውይይት ተደርጓበታል፡፡

በሪፖርቱ በጅማና በጋምቤላ ዮኒቨርስቲዎች  የመማር ማስተማር ሂደቱን ምቹና ሠላማዊ ለማድረግ የተሠሩ ሥራዎችና በተለይ በጅማ ዩኒቨርስቲ የኢንዱስትሪ ዩኒቨርስቲ ትሥሥር ሥራን ውጤታማ ለማድረግ የተሠራውን ሥራ ቋሚ ኮሚቴው በጥንካሬ ተመልክቶታል፡፡

በሁለቱም ዩኒቨርስቲዎች ቁሚ ኮሚቴው በድክምት ከተመለከታቸው ችግሮች መካከል የመምህራን ፍልሰት፣ የመምህራንና የተማሪዎች ግንኙነት ዴሞክራሲያዊ አለመሆን፣ ለሴት ተማሪዎችና ለአካል ጉዳተኞች የሚደረገው ድጋፍ አናሳ መሆን፣ በዮኒቨርስቲው ማህበረሰብ የሚነሱ የመልካመ አስተዳደር ችግሮች፣ የግዥ ሥርአት እንዲሁም የግንባታ ጥራት ችግሮች በሁለቱም ዮኒቨርስቲዎች መጠናቸው ቢለያይም ለመማር ማስተማር ሂደቱ እንቅፋት ናቸው ሲል በሪፖርት አተኩሮባቸዋል፡፡

በተለይ የጋምቤላ ዩኒቨርስቲ አዲስ ከመሆኑ ጋር ተያየዞ የንፁህ መጠጥ ውሃ እጥረት፣ የመመገቢያ ሥፍራ ምቹ አለመሆን ከአካቢው የአየር ፀባይ ጋር ተዳምሮ ችግሩን የከፋ እንደደረገው ነው በሪፖርቱ የተጠቆመው፡፡

በውይይቱ ከሣይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር የተገኙት ዶ/ር ወንድሙ ክፍሌ የጋምቤላ ዩኒቨርስቲን ጨምሮ በሃገሪቱ ያሉ አዳዲስ ዩኒቨርስቲዎችን ከነባር ዩኒቨርስቲዎች ጋር ለማመጣጠን በልዩ  ፓኬጅ የበጀት ድጋፍ በማድረግ እንደሚሠራ ተናግረዋል፡፡

የመስክ ምልከታውን መነሻ በማድረግ ከቀረበው ሪፖርት የታዩ ጠንካራ ጐኖችን ለማስቀጠልና የተለዩ ድክመቶችን በማረም  ለ2ዐ12 የትምህርት ዘመን ጥሩ ግብዓት መገኘቱንም ጠቁመዋል፡፡

በመጨረም የቋሚ ኮሚቴው ሰብሳቢ ወ/ሮ እምዬ ቢተው ሁሉም ዩኒቨርስቲዎች የተመጣጠነ አቅም እንዲኖራቸው በማድረግ በሃገሪቱ ያሉ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ተማሪዎች እኩል እውቀት የዘው ከዩኒቨርስቲ እንደወጡ ሚኒስቴር መ/ቤቱ  በትኩረት ሊሠራ እንደሚገባ አሣስበዋል፡፡