null Committee said Foreign exchange from Animals and crops is low.

ከእንሰሳት እና ከሰብል ምርቶች የተገኘው የውጭ ምንዛሬ ዝቅተኛ መሆኑን በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የግብርና፣አርብቶ አደርና አካባቢ ጥበቃ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ አስታወቀ፣

ቋሚ ኮሚቴው ጥር 29 ቀን 2011 ዓ/ም የግብርና ሚኒስቴርን የስድስት ወራት እቅድ አፈጻጸም ሪፖርት በገመገመበት ወቅት ወደ ውጭ ከተላከው የሰብልና ቡና ምርት ከእቅዱ አንጻር አፈጻጸሙ 64 በመቶ ሲሆን የተገኘው የውጭ ምንዛሬ ገንዘቡም ዝቅተኛ መሆኑን አመላክቷል፡፡

በተመሳሳይም አገሪቱ ከእንሰሳት ሀብት ማግኘት የነበረባትን የውጭ ምንዛሪ በህገ-ወጥ ንግድ ምክንያት ማጣቷን እና በዘርፉም ያልተፈቱ በርካታ ችግሮች መኖራቸውን ቋሚ ኮሚቴው ገምግሟል፡፡

የግብርና ሚኒስቴር ሚኒስትር አቶ ዑመር ሁሴን የግማሽ ዓመት አፈጻጸም ሪፖርቱን ባቀረቡበት ወቅት ግብርናውን ለማዘመን አዳዲስ የሜካናይዜሽን ቴክኖሎጂዎች የተዋወቁ መሆናቸውን ገልጸው 641 የምርት መሰብሰቢያ ኮምባይነሮች እና 381 ሁለገብ መውቂያ ማሽኖች ተሰማርተው በርካታ ምርት መሰብሰቡን አብራርተዋል፡፡

የምርጥ ዘር አቅርቦትን በተመለከተ አምራች ድርጅቶች በ58 ሺህ ሄክታር ላይ የተለያዩ ምርጥ ዘሮችን እንዲያለሙ ተደርጎ 450 ሺህ 971 ኩንታል የተሰበሰበ መሆኑን ሚኒስትሩ ተናግረዋል፡፡

የግብርናውን ምርትና ምርታማነት በእንሰሳት ዘርፉ ለማሳደግ ለአረብቶ አደሮች ሙያተኞች ተመድበው ድጋፍ እየተደረገ እንደሆነ፣ የእንሰሳት ዝርያን ለማሻሻል እና ከእንሰሳት የሚገኘውን ምርት በጥራት በማምረት በአለም ገበያ ተወዳዳሪ ለመሆን ዘርፈ ብዙ ስራዎች እየተከናወኑ መሆኑን ሚኒስትሩ አብራርተዋል፡፡

ቋሚ ኮሚቴው በበኩሉ የእንሰሳት ልማት ዘርፉ  በረካታ ችግሮች እንዳሉበት ገልጾ ለዚሁም በርካታ የመንግስትና የግል ፕሮጀክቶች በአርብቶ አደሩ አካባቢ መገንባታቸው አሉታዊ ተፅዕኖ ማሳደሩንና ማህበረሰቡም ከፕሮጀክቶች ተጠቃሚ እንዳልሆነ አስረድተው ድጋፍ የሚያደርጉ ባላሙያዎችም የእውቀትና ክህሎት ክፍተቶች እንዳለባቸው ተናግረዋል፡፡

የግብርናውን ምርትና ምርታማነት ለማሳደግ በሚደረገው ሁለንተናዊ ርብርብ የማዳበሪያና የምርጥ ዘር አቅርቦቱም ውስንነት እንዳለበት ጠቁመው የተፋሰስና የመስኖ ፕሮጀክቶች ግንባታ መጓተትም አስተዋጽኦ ማበርከቱን ቋሚ ኮሚቴው ገምግሟል፡፡

በሌላ በኩልም ቋሚ ኮሚቴው ሚኒስቴር መስሪሪያ ቤቱ የሪፎርም ስራዎችን በብቃት ለማሳለጥ የሚደርገውን ቅንጅታዊ ስራ፣የኦዲት ግኝት ማስተካከያውን፣ እና ስንዴን በመስኖ ለማምረት የሚደረገውን ትረት በጥንካሬ አንስቷል፡፡

በአንጻሩ ለተጠሪ ተቋማት የሚደረገው ድጋፍ፣ ከግርናው ዘርፍ የሚገኘው ምርት ብዛትና ጥራት ዝቅተኛ መሆኑን እንዲሁም ህገ-ወጥ ንግድን ለመግታት ያለው ቁርጠኝነት አነስተኛ መሆኑን በክፍተት አመላክቷል፡፤

በተመሳሳይም የገጠር የስራ እድል ፈጠራው፣ ለቴክኖሎጂ ተጠዋሚዎች የተሰጠው ስልጠና፣እንዲሁም አርብቶ አደሮችን የኤክስቴንሽን ተጠቃሚ ከማድረግ አንጻር የተሰሩ  ስራዎች ውስንነት እነዳለባቸው ቋሚ ኮሚቴው  ጠቁሟል፡፡