null Employees urged the secretariat to improve its complaint management.

የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ጽህፈት ቤት ሰራተኞች በተቋሙ ውስጥ ቅሬታ የሚፈጥሩ አሰራሮች እንዲሻሻሉ ጠየቁ፡፡

የጽህፈት ቤቱ ሰራተኞች ከጥቅምት 24-25 ቀን 2011 ዓ.ም ለሁለት ቀናት በቢሾፍቱ ከተማ ሲቪል ሰርቪስ ኮሚሽን ባዘጋጀው የትምህርትና ስልጠና ማንዋል እና በምርጥ ተሞክሮ ቅመራ ላይ ስልጠና ከመውሰዳቸው ባሻገር የምክር ቤቱ ጽህፈት ቤት የአንደኛ ሩብ ዓመት  እቅድ አፈጻጸም ሪፖርት ላይም ውይይት አድርገዋል፡፡

በዚህ የስልጠናና የውይይት መድረክ ሰራተኞቹ ስራቸውን በአግባቡ እንዳይወጡ መሰናክል የሆነ በርካታ ቅሬታዎችን አንስተዋል፡፡ በተለይም ለመስክ ስራ በሚወጡበት ወቅት  የሚከፈለው አበል ለዕለት ወጪ የማይበቃ አነስተኛ ከመሆኑ ባሻገር በተመሳሳይ ሰራተኞች መካከል ልዩነት መፍጠሩ፣ የሰራተኞች የካፍቴሪያ አገልግሎት ስርዓት ያልተበጀለትና ባለቤት ማጣቱ፣ የአርበኞች ሕንፃ ለስራ ምቹ ያለመሆኑና በመብራት መቆራረጥ ስራ ማደናቀፉ፣ የሚሰጡ የትምህርት ዕድሎችና ስልጠናዎች ግልጽነትን ያልተላበሱ መሆናቸው እና ሌሎች መሰል  ችግሮች በውይይቱ ወቅት በስፋት  ተነስተዋል፡፡

የምክር ቤቱ ጽህፈት ቤቱ ዋና ፀሐፊ ዶ/ር ምስራቅ መኮንን  ከሰራተኞቹ የተነሱትን ጥያቄዎችና አስተያየቶች ትክክል መሆናቸውን በመቀበል በሚቀጥለው ሩብ ዓመት ዳግም ችግር ሁነው እንዳይከሰቱ ሁሉም የሚመለከተው አካል የበኩሉን ድርሻ በመውሰድ ጠንክሮ መስራት እንዳለበት በጥብቅ አሳስበዋል፡፡

የሩብ ዓመቱ የዕቅድ አፈፃጸም በአስራ አራት ዋና ዋና  ግቦች ላይ ያተኮረ ሲሆን፣ ከእነዚህ ግቦች መካከል የኮሙኒኬሽን አሰራርን ለማሳደግ የተጣለውን ግብ ለማሳካት የሞባይል አፕልኬሽኖች ስርዓት መዘርጋቱ፣ የቴሌ ኮንፌሬንስ ስርዓት መገንባቱና ነፃ የስልክ ጥሪ ማዕከል ለአገልግሎት ዝግጁ መደረጉ ጥሩ አፈፃፀሞች መሆናቸውን ሰራተኛው የተቀበለ ሲሆን የምክር ቤቱን የመሰብሰቢያ አዳራሽ በማደስና የድምፅ ስርዓቱን ዲጅታል ለማድረግ የተሰሩ ስራዎችንም ሰራተኛው በአዎንታዊነት እንደሚመለከት ካቀረቧቸው አስተያየቶች ለመረዳት ተችሏል፡፡

የባለ-ብዙ ዘርፍ ስራዎችን በማሻሻል በኩልም በተለይም ሴቶችን ከማብቃት አኳያ ከሚመለከታቸው ተቋማት ጋር በመተባበር ጽህፈት ቤቱ 62 ሴት ሰራተኞች የትምህርት  እድል እንዳገኙ እንደተመቻቸም በሪፖርቱ ተጠቁሟል፡፡

ለምክር ቤቱ አባላት ለመኖሪያ ከተያዙ ቤቶች ለአባላቱ የማይመጡ ቤቶችን በጊዛዊነት ለጽህፈት ቤቱ ሰራተኞች በማበራታቻ መልክ እንዴት ለማስተላለፍ ረቂቅ የውስጥ መመሪያ ቀርቦ ሰራተኛው ተወያይቶበታል፡፡