null Ethiopian Parliament, WTO delegation discuss Ethiopian accession

ቋሚ ኮሚቴው ከዓለም ንግድ ድርጅት ልዑካን ተወያየ

የካቲት 03 ቀን፣ 2012 ዓ.ም.፣ አዲስ አበባ፤ በኢፌዴሪ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የንግድ እና ኢንዱስትሪ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ፣ ከዓለም ንግድ ድርጅት ልዑካን ጋር ኢትዮጵያ የድርጅቱ አባል በምትሆንበት ቅድመ-ሁኔታ ተወያየ፡፡

በውይይቱ ወቅትም የንግድ ጉዳዮች ንዑስ ኮሚቴ ሰባሳቢ የተከበሩ ዘውዴ ከበደ፤ ኢትዮጵያ የዓለም ንግድ ድርጅት አባል ለመሆን የጀመረችው እንቅስቃሴ ዋል አደር ያለ ቢሆንም ተጠናክሮ መቀጠሉን ገልጸዋል፡፡ አያይዘውም ፓርላማው ሕግ አውጪ እንደመሆኑ፤ የሀገሪቱ ፍላጎት ተሳክቶ በሰነድ የተደገፈ ስምምነት ለማየት እንደሚሹም ጠቁመዋል፡፡

የኢንቨስትሜንት ጉዳዮች ንዑስ ኮሚቴ ሰባሳቢ የተከበሩ አብዱላሂ ሀሙ በበኩላቸው፤ በኢትዮጵያ እና በዓለም ንግድ ድርጅት መካከል የተጀመረው ድርድር ሲያልቅ ስምምነቱን መርምሮ ለማጽደቅ ፓርላማው ዝግጁ መሆኑን አስታውቀዋል፡፡ በተጨማሪም ሀገሪቱ የወጪ እና ገቢ ምርቶችን ከማመጣጠንም ሆነ በሌሎች ምጣኔ-ሀብታዊ ጉዳዮች ከድርጅቱ ማግኘት ያለባትን ልምድ በጥያቄ መልክ አቅርበዋል፡፡

የዓለም ንግድ ድርጅት ምክትል ዋና ዳይሬክተር እና የልዑካኑ መሪ አምባሳደር አለን ዎልፍ ደግሞ፤ ኢትዮጵያ ድርጅቱን ለመቀላቀል ያሳየችውን መነሳሳት አድንቀዋል፡፡ ፓርላማውም ለጉዳዩ የሰጠውን ትኩረት በተመሳሳይ አድንቀው፤ በተያዘበት አኳኋን ከቀጠለ እስከተያዘው የአውሮፓውያኑ ዓመት መጨረሻ ብዙ ጉዳዮች እልባት ሊያገኙ እንደሚችሉ ዕምነት አሳድረዋል፡፡

ኢትዮጵያ የዓለም ንግድ ድርጅት አባል ብትሆን ስለምታገኛቸው ጥቅሞች ሲያስረዱም፤ ሀገሪቱ እ.አ.አ. በ2030 ከአፍሪካ የበለጸጉ ሀገራት አንዷ ለመሆን የያዘቸውን ራዕይ እንድታሳካ ድርጅቱ የበኩሉን ሚና ይጫወታል ብለዋል፡፡ ለምጣኔ-ሀብታዊ ተቋማቶቿም መደበኛ እና ጥራት መሠረት ያደረገ አስተዳደራዊ ድጋፍ ሊያደርግ እንደሚችልም አመላክተዋል፡፡

የኢትዮጵያ መንግስትም ሀገሪቱን የድርጅቱ አባል በማድረግ እና በተጀመረው የለውጥ ርምጃዎች ተንተርሶ፤ የዜጎቹን የኑሮ ደረጃ እና ሀገራዊ ሰላምን ለማስፈን ተጨማሪ ሰፊ ዕድል እንደሚያገኝም ጠቅሰዋል፡፡

ድርጅቱን ለመቀላቀል የሚደረጉትን ጥረቶች የሚያስተባብረውን ክፍል የሚመሩት ወ/ሮ ሜይካ ኦሺካዋ በበኩላቸው፤ ፓርላማው አስፈላጊ የሕግ ማዕቀፎችን ቀድሞ መጨረስ ይገባዋል ብለዋል፡፡ ይህ አካሄድ ወደፊት የሚደረሰውን ስምምነት ለማጽደቅ መሠረት እንደሚጥልም አስገንዝበዋል፡፡ ከዚህም ባሻገር ፓርላማው ዓለም-አቀፍ ልምዶችን ቢቀስም የበለጠ ጥሩ መሆኑንም ጠቁመዋል፡፡

የዓለም ንግድ ድርጅት በሀገራት መካከል የሚካሄደው ንግድ በዓለም-አቀፍ ሕጎች መሠረት እንዲከናወን ያግዛል፤ ድጋፍ ይሰጣል፡፡

በ አሥራት አዲሱ

   የምክር ቤት ፀሐፊ