null FR and PASC urged the Ministry of Peace to continue to promote sustainable peace and security of the nation.

የሰላም ሚኒስቴር በአገሪቱ የጀመረውን ዘላቂ ሰላም የማስፈንና የዜጎችን ደህንነት  የማስጠበቅ ተግባር አጠናክሮ ማስቀጠል እንዳለበት የውጭ ግንኙነትና የሰላም ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ አሳሰበ፡፡

ጥቅምት 26 ቀን 2012 ዓ.ም የሚንስቴሩን የ2012 ዓ.ም ዕቅድና የ3 ወራት የዕቅድ አፈፃፀም ሪፖርት ለቋሚ ኮሚቴው ያቀረቡት ክብርት ሚኒስትር ወ/ሮ ሙፈሪሃት ካሚል ሲሆኑ፤ ዕቅዱ በአገሪቱ ዘላቂ ሰላምን ለማስፈንና የዜጎችን ደህንነት ለማስጠበቅ በሚያስችሉ 20 ግቦች ተከፋፍሎ የቀረበ ነው፡፡

ክብርት ሚንስትሯ የህብረተሰቡን የሰላም ባህል ለማጎልበትና በመሰረታዊ ሀገራዊ ጉዳዮች ላይ መግባባትን ለማሳደግ የሚስችሉ የግንዘቤ ማስጨበጫ ስልጠናዎች ለተለያዩ አካላትና ለበርካታ የህብረተሰብ ክፍሎች መሰጠቱን አብራርተዋል፡፡

ዘላቂ የግጭት መፍትሄ ስርአትን ለማጠናከርና ሰላምን ለማስፈን የተለያዩ ስራዎች መሰራታቸውንና ወደፊትም ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ጠቁመዋል፡፡ በኦሮሚያና በቤኒሻንጉል፣ በኦሮሚያ ጉጂና በደቡብ ብሄር ብሄረሰቦች በጌዲዮ ዞኖች፣ በአማራና በትግራይ፣ በኦሮሚያና በሶማሌ ክልሎች መካከል የተከሰቱ ግጭቶች ቶሎ እንዲቆሙ መደረጉንም በአብነት አንስተዋል፡፡

አክለውም የዜጎችንና የተቋማትን የህግ ማስከበርና ማማከር ተግባርን ማጠናከር፣ ልዩ ድጋፍ የሚያስፈልጋቸውን ክልሎችና አርብቶ አደር አካባቢዎችን የልማት ተጠቃሚነትን የማሳደግ፣ የግጭት ቅድመ ማስጠንቀቂያ ፈጣን ምላሽ ስርአትን ማጠናከር፣ የወንጀል ቁጥጥርና ክትትል ስርአትን ማሻሻል በዕቅዱ ውስጥ ተካተው በመከናወን ላይ መሆናቸውን ገልፀዋል፡፡

በቅርቡ በአገሪቱ አንዳንድ ቦታዎች ተከስተው በነበሩ ግጭቶች ዜጎች እንዲፈናቀሉና ህይወት እንዲጠፋ ያደረጉ እንዲሁም ንብረት የዘረፉና ያወደሙ አካላት ከፌደራል ፓሊስና ከክልሎች ጋር በመሆን የማጣራት ስራ መሰራቱንም ነው ክብርት ሚኒስትሯ ያስረዱት፡፡

ሪፖርቱን አስመልክቶ ከቋሚ ኮሚቴውና ከአባላት በርከት ያሉ ጥያቄዎች የቀረቡ ሲሆን፤ በአገሪቱ አንዳንድ አካባቢዎች በተነሱ ግጭቶችና መፈናቀሎች እንዲሁም አጥፊዎችን አሳልፎ በመስጠት ዙሪያ በአመራሮች የእርስ በርስ ግንኙነት መካከል ችግር መኖሩን የሚያሳይ በመሆኑ ሚንስቴር መስሪያ ቤቱን ይህን ችግር ለመቅረፍ የሚያስችል እቅድና ቁርጠኝነት አለወይ? የሚሉት በዋነኛነት የሚጠቀሱ ናቸው፡፡

የፌደራል ፓሊስ ኮሚሽን ዋና ኮሚሽነር እንደሻው ጣሰው ‹‹የፖሊስ ዋነኛ ተግባር ህገ-መንግስቱንና የዜጎችን ሰላምና ደህንነት መጠበቅ ነው፤ ይሁንእንጂ ተቋሙ ይህን ስራ በሚያከናውንበት ጊዜ አልፎ አልፎ የፖለቲካ ጣልቃ ገብነት ይታያል፡፡›› ብለዋል፡፡

‹‹ተቋሙ አጥፊዎችን የመያዝ እንጂ የመለየት ችግር የለበትም፤ አጥፊዎች በግላቸው አጥፍተው ተጠያቂ ሲሆኑ ዘርና ሀይማኖት ውስጥ ስለሚወሸቁ ሂደቱን አስቸጋሪ አድርጎታል›› ብለዋል፡፡

ሆኖም በአገር ውስጥ የሚገኙ የወንጀል ተጠርጣሪዎችን ከክልሎች ጋር በመሆን፣ በውጭ የሚገኙትን ደግሞ ከኢንተር ፖል ጋር በመፃፃፍ ተጠያቂ ለማድረግ እየተሰራ መሆኑን፣  ለስኬታማነቱ ህብረተሰቡና የሚመለከተው አካል ሁሉ ድጋፍ ማድረግ እንዳለበትም ነው ያብራሩት፡፡

የሰላም ሚንስትሯ ክብርት ወ/ሮ ሙፈሪሃት ካሚል በበኩላቸው በአገሪቱ እየታዩ ያሉ ችግሮች ለበርካታ ዓመታት ሲንከባለሉ የመጡ በመሆናቸው በአንድ ጀንበር ሊፈቱ እንደማይችሉ፤ ነገር ግን ሚንስቴር መ/ቤቱ ከዚህ በላይ ጉዳት እንዳይደርስ በርካታ ስራዎችን በቁርጠኝነት መስራቱ ሊታወቅ እንደሚገባ እና ወደፊትም ከህዝቡ ጋር በመሆን ስራውን አጠናክሮ እንደሚቀጥል ምላሽ ሰጥተዋል፡፡

የውጭ ግንኙነትና የሰላም ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ የተከበሩ አቶ ተስፋዬ ዳባ በሰጡት ማጠቃለያ ሚኒስቴር መ/ቤቱ የተቋሙን ውስጣዊና ውጪያዊ፣ አገራዊና አለማቀፋዊ ሁኔታዎችን በመተንተን ዕቅዱን ማዘጋጀቱ እና የህብረተሰቡን አገር በቀል የሰላም ዕሴቶችን በዕቅዱ ውስጥ ማካተቱን በጥንካሬ አንስተዋል፡፡

በሌላ በኩል በሚንስቴር መ/ቤቱ ስር የሚገኙና የህብረተሰቡ ሰላምና ደህንነት ለማስጠበቅ በርካታ ስራዎችን እየሰሩ ያሉ ተጠሪ ተቋማትን ከመደገፍ ባሻገር ምን እየሰሩ እንደሆነና ህብረተሰቡም ስለእነሱ ምን እንደሚል ጆሮ ሰጥቶ ማዳመጥና አሰራራቸውንም በትኩረት መፈተሽ እንደሚያስፈልግ አስገንዝበው፤ አሁንም ያልተፈቱ ፖለቲካዊ ጥያቄዎችን ከምክር ቤቱ ጋር በመሆን መፍታት እንደሚገባም ነው ያሳሰቡት፡፡