null House passed Amendment of the Houses Secretariat Establishment proclamation.

የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ጽ/ቤት ቤት የራሱን ሚዲያ እንዲያቋቁም እና የጥናት፣ የምርምርና የማማከር ስራዎችን እንዲያከናውን የሚያስችል አዋጅ ፀደቀ፡፡

አምስተኛው የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በአራተኛ የስራ ዘመኑ ጥር 29 ቀን 2011 ዓ.ም ባደረገው 3ኛ ልዩ ስብሰባው የምክር ቤቱን ጽህፈት ቤት ማቋቋሚያ አዋጅ ቁጥር 906/2007ን ለማሻሻል የቀረበ ረቂቅ አዋጅን መርምሮ አፅድቋል፡፡

የምክር ቤቱ ጽ/ቤት በ1988 ዓ.ም በአዋጅ ቁጥር 53/88 ተቋቁሞ ለምክር ቤቱ ሙያዊ ድጋፍና አስተዳደራዊ አገልግሎት እየሰጠ እስከአሁን ድረስ የቆየ የፌዴራል ተቋም ሲሆን በነዚህ ጊዜያት ውስጥ ከወቅቱ ፍላጎቶች ጋር ተልዕኮው እንዲጣጣም ለማስቻል የማቋቋሚያ አዋጁ ሶስት ጊዜ ተሻሽሏል፡፡

አሁን ማሻሻያ የተደረገለት አዋጅ ቁጥር 906/2007 ለምክር ቤቱ ጽህፈት ቤት የሰጠው ስልጣንና ተግባር፤ ለምክር ቤቱ ህግ አወጣጥ፣ ክትትልና ቁጥጥር እንዲሁም ለውክልና ስራ የሚያገለግሉ ሙያዊ ድጋፍ እና አስተዳደራዊ አገልግሎቶችን መስጠት፣ ለምክር ቤቱና ምክር ቤቱ ለሚያቋቁማቸው ኮሚቴዎችና ውስጣዊ አካላት አጠቃላይ ሙያዊ ድጋፍና አስተዳደራዊ ግልጋሎቶችን መስጠት፣ የፌዴራል ነጋሪት ጋዜጣን ማስተዳደር፣ የምክር ቤቱን የህዝብ ግንኙነት ተግባራት ማከናወን፣ ለምክር ቤቱ አባላት እና አካላት በህግ የተወሰኑ ጥቅማጥቅሞችን እና ልዩ መብቶችን ማስፈፀም ወዘተ የሚሉ ናቸው፡፡

የአሁኑ ማሻሻያ በከፊል ለምክር ቤቱ ጽህፈት ቤት ከተሰጡት ስልጣንና ተግባር በተጨማሪ የምክር ቤቱ ጽህፈት ቤት የምክር ቤቱን ስራዎች ለህዝብ ተደራሽነት የበለጠ ለማስፋት አቢይ አማራጭ የሆነውን የሚዲያ አገልግሎት በራሱ አቋቁሞ ተግባሩን የተሳለጠ ለማድረግና የሚወጡ ህጎች ለህዝብ በፍጥነት እንዲደርስ ከፍተኛ አስተዋፅኦ ያለው መሆኑን ረቂቁን የመረመረው የሰው ሀብት ልማትና ቴክኖሎጂ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ በለያቸው ዋና ዋና ጭብጦች ውስጥ ተመላክቷል፡፡

ቋሚ ኮሚቴው ስለማሻሻያ ህጉ ሌላውን ጭብጥ ሲያስቀምጥ፤ በቀድሞው የጽህፈት ቤቱ ማቋቋሚያ አዋጅ ላይ የምክር ቤቱ ጽህፈት ቤት የጥናትና የምርምር ስራዎችን እንደሚያከናውን በግልፅ ያልተቀመጠ በመሆኑ በደረጃ ምዘናም ሆነ ሌሎች ጉዳዮች ያጋጥሙ የነበሩ ችግሮችን በማስቀረት የጥናት፣ ምርምርና የማማከር ስራን በጽህፈት ቤቱ ስልጣንና ተግባር ውስጥ ማካተቱ ነው፡፡

ሶስተኛው ጭብጥ፤ ማሻሻያ ህጉ የፌዴራል ሲቪል ሰርቪስ አስተዳደር መርሆዎችን ጠብቆ የምክር ቤቱ ጽህፈት ቤት የተሰጡትን ተግባርና ሃላፊነት ለመወጣት የሚያስችሉትን ከፍተኛ ባለሙያዎች ከገበያ ለማግኘት እንቅፋት ሆኖበት የነበረውን የሰው ቅጥር፣ ደመወዝና ጥቅማጥቅም ጉዳዮች ለመፍታት ምክር ቤቱ በራሱ እንዲወስን የሚያስችል መሆኑ ነው፡፡

ከዚህ በተጨማሪ በማሻሻያው የምክር ቤቱ ጽህፈት ቤት ዋና ፀሐፊ ሹመትም ምክር ቤቱን በበላይነት ለሚመራው አፈ ጉባኤ ስልጣኑን ሰጥቷል፤ በቀድሞው አዋጅ ላ አፈ ጉባኤው የተለያዩ አካላትን እንዲያማክር የተጣለበትን ግዴታም ተነስቷል፡፡

በቀረበው የቋሚ ኮሚቴው ሪፖርትና የውሳኔ ሃሳብ ላይ የምክር ቤቱ አባላት የተወያዩ ሲሆን አንዳንድ የምክር ቤቱ አባላት የምክር ቤቱ ጽህፈት ቤት በፌዴራል ሲቪል ሰርቪስ ተቋም ስር መተዳደሩ እንዲቀጥል ሃሳብ አራምደዋል፡፡

በመጨረሻም ም/ቤቱ ማሻሻያ ረቂቅ አዋጁ አዋጅ ቁጥር 1114/2011 ሆኖ በ19 ተቃውሞ እና በ31 ተአቅቦ በአብላጫ ድምፅ አፅድቆታል፡፡

ከዚህ በተጨማሪ ምክር ቤቱ የህግ፣ ፍትህና ዴሞክራሲ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎትን እንደገና ለማቋቋም ያቀረበውን ሪፖርትና የውሳኔ ሃሳብ መርምሮ ረቂቅ አዋጁ አዋጅ ቁጥር 1115/2011 ሆኖ በሙሉ ድምፅ ደግፎ አፅድቆታል፡፡

በተመሳሳይም ም/ቤቱ ከአልጀሪያ ህዝባዊ ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ ጋር በእንስሳትና አሳ ሀብት ልማት ዘርፍ የተፈረመውን የመግባቢያ ስምምነት ረቂቅ አዋጅ እና የሁለትዮሽ የንግድ ስምምነት ማፅደቂያ ረቂቅ አዋጅ ላይ የውጭ ግንኙነትና ሰላም ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ በጋራ ያቀረቡትን ሪፖርትና የውሳኔ ሃሳብ መርምሮ በቅደም ተከተል አዋጅ ቁጥር 1115/2011 እና አዋጅ ቁጥር 1116/2011 ሆኖ እንዲፀድቅ በሙሉ ድምፅ ወስኗል፡፡