null Houses put off Census for the third time

በሀገሪቱ አሁን ባለው የኮቪድ 19 ወረርሽኝ ምክንያት 4ኛውን የህዝብና ቤት ቆጠራ ማድረግ እንደማይቻል ተገለጸ

 

የኢፌዴሪ የህዝብ ተወካዮችና የፌዴሬሽን ም/ቤቶች ባደረጉት የጋራ ውይይት አራተኛውን የህዝብና ቤት ቆጠራ ለሶስተኛ ጊዜ ለማራዘም የቀረበውን የውሳኔ ሀሳብ በተናጠልና በጋራ መርምረው አፅድቀዋል፡፡

 

ፓርላማ ሰኔ 04 ቀን 2012 .ም፤ የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዲሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ 5ኛው የሕዝብ ተወካዮች /ቤት ባካሄደው 16 መደበኛ ስብሰባው በተለያዩ አጀንዳዎች ላይ ሲመክር ውሎ ውሳኔዎችን አሳልፏል፡፡

 

ም/ቤቱ በተናጠል ባደረገው ውይይት አራተኛውን የህዝብና ቤት ቆጠራ ለሶስተኛ ጊዜ ለማራዘም ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እና ለፌዴሬሽን ምክር ቤት የጋራ ስብሰባ የተዘጋጀውን የውሳኔ ሀሳብ የም/ቤቱ አፈ-ጉባኤ የተከበሩ አቶ ታገሰ ጫፎ በአገሪቱ አሁን ባለው የኮቪድ 19 ወረርሽኝ ምክንያት 4ኛውን የህዝብና ቤት ቆጠራ ማካሄድ እንደማይቻልና አገሪቱ አሁን ካለው ወረርሽኝ ነጻ መሆኗን የሚመለከታቸው አካላት እስኪያረጋግጡ ድረስ እስከ 2 ዓመት ድረስ ቆጠራው ለ3ኛ ጊዜ እንዲራዘም አቅርበዋል፡፡

 

ም/ቤቱ በአጀንዳው ላይ ከተወያየ በኋላ የቀረበውን የውሳኔ ሀሳብ ቁጥር 10/2012 ሆኖ በ8 ተቃውሞና በ12 ድምጸ ተአቅቦ በአብላጫ ድምፅ አፅድቋል፡፡

 

በተመሳሳይ ዜናም የኢፌዴሪ የህዝብ ተወካዮችና የፌዴሬሽን ም/ቤቶት ባደረጉት 1ኛው ልዩ የጋራ ስብሰባም በአጀንዳው ላይ በስፋት ተወያይተዋል፡፡

 

የጋራ ውይይቱን የመሩት አዲስ የተሾሙት የፌዴሬሽን ም/ቤት አፈ-ጉባኤ አቶ አደም ፋራህ አራተኛውን የህዝብና ቤት ቆጠራ በአገሪቱ አሁን ባለው የኮቪድ 19 ወረርሽኝ ባስከተለው ተፅእኖ ምክንያት ማድረግ ባለመቻሉ ቆጠራው ለ3ኛ ጊዜ እንዲራዘም የቀረበውን የውሳኔ ሀሳብ ለሁለቱ ም/ቤቶች በጋራ አቅርበዋል፡፡          

 

የተከበሩ ወ/ሮ ሙሉ ገ/እግዚአብሄር ቆጠራውን ለማራዘም ያስገደዱ ምክንያቶች ሳይዘረዘሩና በቂ ጥናት ሳይደረግ ቆጠራውን ማራዘም ተገቢ እንዳልሆነ አስተያየታቸውን አቅርበዋል፡፡

 

የተከበሩ አቶ ተስፋዬ ዳባ እና የፌዴሬሽን ም/ቤት አባል የሆኑት አቶ ላቀ አያሌው በበኩላቸው የኮቪድ 19 ወረርሽኝ ታላላቅ የሆኑ የአለም አገራት ፈተና በመሆኑ በሀገሪቱም የበሽታው ስርጭት ከቀን ወደ ቀን እየከፋና በርካታ ዜጎች በበሽታው እየተያዙ ባለበት ተጨባጭ ሁኔታ ሌላ ጥናት የሚያስፈልገው ባለመሆኑ አራተኛው የህዝብና ቤት ቆጠራ እንዲራዘም የቀረበው ጥያቄ ተገቢነት ያለው መሆኑን አብራርዋል፡፡

 

ሁለቱ ም/ቤቶች በአጀንዳው ላይ በስፋት ከተወያዩበት በኋላ አራተኛውን የህዝብና ቤት ቆጠራ ለሶስተኛ ጊዜ ለማራዘም ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እና ለፌዴሬሽን ምክር ቤት የጋራ ስብሰባ የተዘጋጀው የውሳኔ ሀሳብ ቁጥር 1/2012 ሆኖ በ5 ተቃውሞ እና በ13 ድምጸ ተአቅቦ በአብላጫ ድምፅ በጋራ ጸድቋል፡፡