null Inquiry Board approved its filed observation report

አስቸኳይ ጊዜ አዋጅ አፈፃፀም መርማሪ ቦርድ ያካሄደውን የመስክ ምልከታ በተመለከተ በተዘጋጁት ሪፖርቶች ላይ ተወያይቶ ሪፖርቶቹን አፅድቋቸዋል፡፡

ሚያዚያ 26 ቀን 2012 ዓ.ም (ዜና ፓርላማ) ቦርዱ ባካሄደው ሳምንታዊ ስብሰባው የትራንስፖርት ባለስልጣን እና የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የኮሮና ቫይረስን ለመከላከልና ለመቆጣጠር መንግስት ያወጣውን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ተፈጻሚ ለማድረግ እያከናወኑ ያሉትን ተግባራት በመስክ ምልከታው መቃኘቱ ተከትሎ በተዘጋጁት የአፈጻፀም ሪፖርቶች ላይ በዝርዝር ተወያይቷል፡፡

የቦርዱ ሰብሳቢ የተከበሩ አቶ ጴጥሮስ ወ/ሰንበት ቦርዱ ወደ ስራ ከገባ ጊዜ ጀምሮ በርካታ ተግባራትን በማከናወን የተሰጠውን ሃላፊነት በመወጣት ላይ እንደሚገኝ ገልጸዋል፡፡

በፌደራል ትራንስፖርት ባለስልጣን የተደረገውን የመስክ ምልከታ አስመልክቶ የተዘጋጀውን ሪፖርት ያቀረቡት የተከበሩ ወ/ሮ ሞሚና መሀመድ ባለስልጣኑ አዋጁን ለማስፈጸም ያከናወናቸውን ጠንካራ አፈፃፀሞች እና በክፍተት የተለዩ ተግባራትን በዝርዝር አቅርበዋል፡፡

ባለስልጣኑ ከሚመለከታቸው ተቋማት የተውጣጣ ግብረ ሀይል፣ የቴክኒክ እና ንሳን ኮሚቴዎችን በማቋቋም ወደ ስራ መግባቱ፣ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ማስፈፀሚያ፣ ደንብና የትራንስፖርት ሚ/ር ያወጣውን መመሪያ ልዩ ልዩ የሚዲያ ስልቶችን በመጠቀም ህብረተሰቡ እንዲያውቃቸው መደረጉ፣ ሙሉ እና ጎደሎ የታርጋ ቁጥር ያላቸው ኮድ 2 ተሽከርካሪዎች በፈረቃ እንዲንቀሳቀሱ መደረጉን ተከትሎ ኮቪድ 19ን በመከላከል ስራ ላይ ለተሰማሩ አካላት እንዲሁም ለአካል ጉዳተኞችና የኩላሊት እጥበት ለሚያደርጉ ግለሰቦች ተመሳስሎ ሊሰራ የማይችል የይለፍ ካርድ መዘጋጀቱን በጠንካራ አፈጻፀም አንስተዋል፡፡

በሌላ በኩል የዕለት የትራንስፖርት ስምሪት 50% መሆን እንዳለበት ቢቀመጥም ከተፈቀደው በላይ ትርፍ ሰው በመጫን፣ ከታሪፍ በላይ በማስከፈል፣ ከክልሎችና ከከተማ አስተዳደሩ እንዲሁም ከሚመለከታቸው አካላት ተቀናጅቶ በመስራቱ ረገድ ከፍተቶች የሚታዩና በቀጣይም ባለስልጣኑ ትኩረት ሰጥቶ ሊሰራባቸው የሚገቡ መሆኑን ባቀረቡት ሪፖርት አመላክተዋል፡፡

የቦርዱ አባላትም በመስክ ምልከታው የተስተዋሉ በጠንካራና በቀጣይ ትኩረት ሊደረግባቸው ይገባል ያሏቸውን ተጨማሪ ነጥቦች በሪፖርቱ ውስጥ እንዲካተቱ አንስተዋል፡፡

የቦርዱ ም/ሰብሳቢ የተከበሩ አቶ ተስፋዬ ዳባ ከአባላቱ የተነሱ ነጥቦች ሪፖርቱን ይበልጥ የሚያዳብሩ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡ ቦርዱም ሪፖርቱን ተቀብሎ በሙሉ ድምጽ አፅድቆታል፡፡                 

በተያያዘም የተከበሩ ወ/ሮ ፋንታዬ ወንድም የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በአገሪቱ የተከሰተውን የኮሮና ቫይረስ ስርጭትን ለመከላከልና ለመቆጣጠር እንዲሁም የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን ለማስፈጸም ያከናወናቸውንና በማከናወን ላይ የሚገኙትን ተግባራት መነሻ በማድረግ የተዘጋጀውን ሪፖርት አቅርበዋል፡፡

የከተማ አስተዳደሩ የቫይረሱን ስርጭት ለመከላከልና ለመቆጣጠር የሚያስችል አደረጃጀት ከላይኛው እስከ ታችኛው መዋቅር ድረስ መፍጠሩ እና አፈፃፀሙንም በየጊዜው እንዲገመገም ማድረጉ፣ ከተለያዩ የሙያ ዘርፎችና ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በቅንጅት መስራቱ፣ የተፈጠረውን ሁኔታ መነሻ በማድረግ በነዋሪው ላይ ያልተገባ የዋጋ ጭማሪ እንዳይደረግ ተገቢው የንግድ ቁጥጥር መደረጉ፣ ወረርሽኙ በከተማዋ ነዋሪዎች ላይ የከፋ ጉዳትና የኢኮኖሚ ጫና እንዳያስከትል ሀብት ማሰባሰብን ጨምሮ ተገቢው ቅድመ ዝግጅት መደረጉን ከጠንካራ አፈፃፀሞች ውስጥ በዋናነት እንደሚገኙበት በሪፖርቱ ገልጸዋል፡፡

ይሁን እንጂ በከተማዋ የትራንስፖርት አገልግሎቶች እጥረት መከሰት፣ ህዝብ በሚበዛባቸው ሀይማኖታዊ ተቋማት፣ የገበያ ቦታዎች እንዲሁም የትራንስፖርት አገልግሎት መስጫ ቦታዎች ላይ ተሳፋሪዎች ላይ የሚስተዋል አካላዊ ርቀትን ያለመጠበቅ፣ የአፍና የአፍንጫ መሸፈኛ ማስኮችን ያለመጠቀም እና በከተማዋ ከተዘጋጁ የለይቶ ማቆያዎች በተወሰኑት ላይ የውሀና የመብራት አቅርቦት እጥረት መኖሩን በሪፖርቱ ውስጥ በውስንነት አንስተዋል፡፡

የቦርዱ አባላትም በቀረበው ሪፖርት ላይ በስፋት ከተወያዩና ግብአት ከሰጡ በኋላ ሪፖርቱን በሙሉ ድምፅ አፅድቀዋል፡፡

በመቀጠልም ቦርዱ በቀረበው የቦርዱ የአሰራር እና የአባላት የስብሰባ ስነ ስርዓት መመሪያ ላይ የመከረ ሲሆን፤ የቦርዱ የስብሰባ ቀናት በሳምንት 2 ጊዜ እንደሆነ፣ መመሪያው በቦርዱ አባላትና በድጋፍ ሰጪ ባለሙዎች ላይ ከሚያዚያ 26 ቀን 2012 ዓ.ም ጀምሮ ተፈፃሚ እንደሚሆን ተቀምጧል፡፡

የኮቪድ 19 ስርጭትን ለመከላከልና ለመቆጣጠር የወጣው አስቸኳይ ጊዜ አዋጅ አፈጻፀም መርማሪ ቦርድ የአሰራር እና የአባላት የስብሰባ ስነ-ስርዓት መመሪያ ቁጥር 1/2012 ሆኖም በሙሉ ድምጽ ፀድቋል፡፡

በውይይቱ መጨረሻም ቦርዱ ቀጣይ የስራ አቅጣጫዎችን አስቀምጧል፡፡

ዘጋቢ:- ኃ/ሚካኤል አረጋኸኝ