null It was told that the challenges facing the Minority Regions and pastoralists should be finalized.

ምክር ቤቱ ባካሄደው 31ኛ መደበኛ ስብሰባ የፌዴራልና የአርብቶ አደር ልማት ጉዳዮች ሚኒስቴር የ2010 በጀት ዓመት የ11 ወራት እቅድ አፈጻጸም ሪፖርትን አዳምጧል፡፡

የፌዴራልና የአርብቶ አደር ልማት ጉዳዮች ሚንስቴር ሚንስትር አቶ ከበደ ጫኔ ባቀረቡት ሪፖርት እንደገለጹት በህግ መንግስቱና በህብረ ብሄራዊ ፌዴራል ስርዓታችን ባህሪያት ዙሪያ ያለው ሀገራዊ ግንዛቤና ብሄራዊ መግባባት በመሚፈለገው ደረጃ ላይ ባለመድረሱ ስርዓቱ የግጭት መንስኤ ነው የሚል የተሳሳተ አመለካከት ስለሚስተዋል በቀጣይ ትልቅ የማስተካከያ ስራ የሚያስፈልገው መሆኑን ተናግረዋል፡፡

በሌላ በኩልም በግጭት መከላከልና አፈታት እንዲሁም ከሰላም እሴት ግንባታ አኳያ የግጭት ቅድመ ማስጠንቀቂያና ፈጣን ምላሽ የመስጠት ስርዓቱ ያልተጠናከረ መሆን፣ በአስተምህሮት ስራዎች ላይ አመርቂ ውጤት ማምጣት አለመቻሉ እና የወሰን ማካለል ጉዳዮችን በፍጥነት እልባት አለመስጠት የዘርፉ ዋና ዋና ተግዳሮቶች መሆናቸውን ሚንስትሩ አስረድተዋል፡፡

የአዲስ መንደር ማሰባሰብ እቅድ አፈጻጸም ዝቅተኛ የሆነበት ምክንያት በፌዴራና በሁሉም ታዳጊ ክልሎች የሚገኙ የአመራሮችና የባለሙያዎች ቁርጠኝነት መጓደል እንዲሁም የልማት ፕሮጀክቶች በተቀመጠላቸው ጊዜ አለመጠናቀቅ ተጠቃሾች ናቸው ሲሉም ሚኒስትሩ ገልጸዋል፡፡

የምክር ቤት አባላት በበኩላቸው በታዳጊ ክልሎችና በአርብቶ አደሩ አካባቢ የሚገነቡ ትላልቅ ሜጋ ፕሮጀክቶች ህብረተሰቡን ተጠቃሚ እያደረጉ እንዳልሆነና ለሴቶች የሚደረገው ሁለንተናዊ ድጋፍ አናሳ መሆኑን አስገንዝበው በተለያዩ አካባቢዎች ለሚነሱ ግጭቶች ዘላቂ መፍትሄ መፈለግ እንጂ በየጊዜው እሳት የማጥፋት አይነት ስራ መሰራት እንደሌለበትም አሳስበዋል፡፡

የፌዴራልና አርብቶ አደር ልማት ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ የተከበሩ ወ/ሮ ፈቲያ የሱፍ በበኩላቸው በአገሪቱ በተለያዩ አካባቢዎች ግጭቶች በተከሰቱበት ወቅት ውጥረቱን ለማርገብ በ23 ዩኒቨርሲቲዎች ውይይት መካሄዱ፣ ከሚዲያዎች ጋር በመተባበር የህብረተሰቡን ባህል ለመገንባት በተለያዩ ቋንቋዎች መልዕከክቶች ተቀርጸው መተላለፋቸውና ስለ ግጭት አፈታት ጥናታዊ ጽሁፎች መቅረባቸውን በጠንካራ ጎን ገልጸው፣ በአንጻሩ በፌዴራሊዝም አስተምህሮ፣ በመንደር ማሰባሰብ እና የወሰን ማካለል ስራው አለመፋጠን በክፍተት የታዩ አበይት ነጥቦች መሆናቸውን አስረድተዋል፡፡

በመጨረሻም ም/ቤቱ የምክር ቤቱን የ3ኛ ዓመት የስራ ዘመን 30ኛ መደበኛ እና የ4ኛውን ልዩ ስብሰባ ቃለ ጉባኤዎች ያለ ምንም ተቃውሞና ድምጽ ተዓቅቦ በሙሉ ድምጽ አፅድቋል፡፡